Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

42 ባለሃብቶች በቡልቡላ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመሰማራት ውል ፈፅመዋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 42 ባለሃብቶች በቡልቡላ የተቀናጀ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመሰማራት ውል መፈፀማቸውን የኦሮሚያ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

የኦሮሚያ ክልል የተለያዩ የስራ ኃላፊዎችና ባለሃብቶች የቡልቡላ የተቀናጀ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎብኝተዋል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሰናይት መብሬ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት፥ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን አሟልቶ የያዘው ፓርኩ ባለሃብቶችን ተቀብሎ እያስተናገደ ይገኛል።

በፓርኩ ለመሰማራት ውል ከፈጸሙ አምስቱ ወደ ስራ በመግባት 11 ዓይነት የግብርና ምርቶችን እያቀነባበሩ ነው ብለዋል።

ቀሪ 37ቱም ስራ ለመጀመር ከኦሮሚያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን ገልጸዋል።

ሁሉም ባለሃብቶች ሙሉ ለሙሉ ስራ ሲጀምሩ ከ16 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥሩ መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

በምስራቅ ሸዋ ዞን በ271 ሔክታር መሬት ላይ በየተገነባው የቡልቡላ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፓርክ፥ የግብርና ምርቶችን እሴት ጨምሮ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ማቅረብን ዓላማ ያደረገ ነው።

Exit mobile version