ስፓርት

በአውሮፓ ዋንጫ እንግሊዝ ከስዊዘርላንድ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል

By Shambel Mihret

July 06, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአውሮፓ ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ መርሐ ግብር እንግሊዝና ስዊዘርላንድ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡

የ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ መርሐ ግብር ዛሬ ምሽት በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጠናቀቃል።

በዚህም መሰረት እንግሊዝ ከስዊዘርላንድ ምሽት 1:00 ላይ በዱሴልዶርፍ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡

በጥሎ ማለፉ መርሃ ግብር ስሎቫኪያን 2 ለ 1 በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀለችው እንግሊዝ፤ የ2020 ሻምፒዮኗን ጣሊያንን 2 ለ 0 በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜውን ከተቀላቀለችው ስዊዘርላንድ ብርቱ ፉክክር እንደሚጠብቃት ተገምቷል።

ሌላው የምሽቱ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ በኔዘርላንድስ እና በቱርክ መካከል ምሽት 4:00 ላይ በበርሊን ኦሎምፒክ ስታዲየም ቀጥሎ ይካሄዳል።

በ16ቱ የጥሎ ማለፍ ግጥሚያዋ ሮማኒያን 3 ለ 0 በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀለችው ኔዘርላንድስ፤ ኦስትሪያን 2 ለ 1 በማሸነፍ ከውድድሩ ውጪ ካደረገቻት ቱርክ ብርቱ ፈተና እንደሚጠብቃት ተነግሯል።

በቱርክ በኩል ኦስትሪያ ላይ ሁለት ጎሎችን ያስቆጠረው ተከላካዩ መሪህ ደሚራል በስነ-ምግባር ግድፈት በተላለፈበት ቅጣት ምክንያት የዛሬው ጨዋታ ያመልጠዋል፡፡ በሌላ በኩል ቱርካዊው የ19 ዓመቱ ታዳጊ አርዳ ጉሌር በጨዋታው ግንባር ቀደሙ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

ትናንት ምሽት በተካሄዱ ሁለት የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች አዘጋጇ ጀርመን በስፔን እንዲሁም ፖርቹጋል በፈረንሳይ ተሸንፈው ከውድድሩ ውጪ መሆናቸው ይታወቃል።

በዚህም መሰረት በግማሽ ፍፃሜው ፈረንሳይ ከስፔን የሚፋለሙ ሲሆን፤ ዛሬ የሚካሔዱት ሁለት ጨዋታዎች አሸናፊዎች እርስበርስ የሚገናኙ ይሆናል፡፡