Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የ«ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም» የጎዳና ላይ ሩጫ እስከሚጠናቀቅ ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶች ይፋ ሆኑ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የ«ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም» የጎዳና ላይ ሩጫ መርሐ ግብር ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶች ይፋ ተደረጉ፡፡

የ«ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም» የጎዳና ላይ ሩጫ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ከተማ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ እንደሚደረግ የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል፡፡

ነገ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም የሰላም ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ከተማና ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር «ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም» በሚል መሪ ቃል ያዘጋጁት የጉዳና ላይ ሩጫ በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡

ሩጫው መነሻውን መስቀል አደባባይ በማድረግ በባምቢስ፣ በዑራኤል አደባባይ ወደ ቀኝ፣ ፒኮክ መናፈሻ፣ ሰላም መንገድ፣ በወሎ ሰፈር፣ ደንበል፣ ፍላሚንጎ በማድረግ መስቀል አደባባይ የሚጠናቀቅ ይሆናል ተብሏል፡፡

መርሐ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ዋና መንገዶችን የሚያካልል በመሆኑ፡-

• ከ22 ወደ ዘሪሁን ህንፃ

• ከዘሪሁን ህንፃ ወደ ዑራኤል አደባባይ

• ከአትላስ መብራት ወደ ዑራኤል አደባባይ

• ከቦሌ ሩዋንዳ መታጠፊያ ወደ ወሎ ሠፈር

• ከወሎ ሠፈር ጀምሮ እስከ ጋዜቦ አደባባይ ውስጥ ውስጡን ወደ ዋናው መንገድ የሚያስወጡት መንገዶች

• ከጋዜቦ አደባባይ ወደ ኦሎምፒያ አደባባይ

• ከኤግዚብሽን ወደ ፊላሚንጎ

• ከጥላሁን አደባባይ ወደ መስቀል አደባባይ

• ከለገሃር መብራት ወደ መስቀል አደባባይ

• ከቴሌ ማቋረጫ (ክቡ) ባንክ ወደ ስታድየም

• ከሀራምቤ መብራት ወደ መስቀል አደባባይ

• ከብሔራዊ ቤተ መንግስት ወደ መስቀል አደባባይ

• ከካዛንቺስ ሼል (ኢንተር ኮንትኔታል ሆቴል) ወደ ባምቢስ

• ከዑራኤል አደባባይ ላይ እና ታች ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስዱ መንገዶች ከንጋቱ 11:30 ሰዓት ጀምሮ ፕሮግራሙ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ለተሽከርካሪ ዝግ መሆናቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

ለዚሁ ፕሮግራም ሲባል ከሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ምሽት ከ12 ሰዓት ጀምሮ በተጠቀሱ መንገዶች ላይ ተሽከርካሪን አቁሞ መሄድ የተከለከለ መሆኑንም ፖሊስ ጨምሮ አስታውቋል።

 

 

Exit mobile version