Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አስጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የመዲናዋን የዘንድሮ አረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር በኮልፌ ክፍለ ከተማ መንዲዳ አካባቢ በይፋ አስጀመረዋል።

ከንቲባዋ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በጋራ መስራት፣ መተባበርና በጋራ መቆም የሚያመጣውን ለውጥ የተመለከትንበት ነው ብለዋል።

በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት የከተማዋ የደን ሽፋን በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ መሰረት ወደ 30 በመቶ ለማሳደግ በላቀ ትጋት እንሰራለን በማለት ገልጸው፤ ከተማዋን አረንጓዴ የለበሰች እናደርጋታለን ሲሉ ገልጸዋል።

በተባበረ ክንድ ለመጭው ትወልድ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የምትችል ለም ኢትዮጵያን እናስረክባለን ብለዋል።

በዘንድሮ መርሐ-ግብር 20 ሚሊዮን ችግኞችን በከተማዋ እንደሚተከልም ጠቁመዋል።

በአምስት ዓመቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር መዲናዋን ውበት ያላበሱ እፅዋቶች መተከላቸውን አስታውሰው፤ በዚህም 2 ነጥብ 8 በመቶ ብቻ የነበረው የከተማዋ የደን ሽፋን ወደ 17 በመቶ ከፍ ማለቱን ተናግረዋል።

በመርሃግብሩ ላይ በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ከተማ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሞገስ ባልቻ፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ክፍሎች፣ የከተማዋ የውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ ይመኙሻል ታደሰ ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች፣ አትሌቶችንና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

በመዲናዋ ባለፉት 5 ዓመታት 58 ነጥብ 2 ሚሊዮን ችግኞች የተተከሉ ሲሆን የጽድቀት መጠኑም 89 በመቶ ነው ተብሏል።

በመሳፍንት እያዩ እና በመራኦል ከድር

Exit mobile version