አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሲዳማ ክልል ሆኖ ከተደራጀ ወዲህ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በተከናወነ ሥራ አመርቂ ውጤት መመዝገቡ ተገልጿል፡፡
“ውጤታማ የሥራ ዕድል ለኢኮኖሚያችን ዕድገት” በሚል መሪ ሃሳብ በክልሉ ሥራ ክህሎትና ኢንተርፕራይዞች ቢሮ የተዘጋጀ ኤግዚቢሽንና ባዛር በሃዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።
ባዛሩ ኢንተርፕራይዞችን ለማነቃቃት በሲዳማ ክልል ሥራ ክህሎትና ኢንተርፕራይዞች ቢሮ የተዘጋጀ ሲሆን ፥ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ መርቀው ከፍተውታል ።
አቶ ደስታ ሌዳሞ በመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ፥ እስካሁን በተሰራው ሥራ በርካታ አምራች ኢንተርፕራይዞችን መፍጠር ተችሏል ።
የተዘጋጀው ባዛር ለገበያ ትስስር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው÷ ኢንተርፕራይዞቹ ጠንክረው እንዲሰሩ ጠይቀዋል ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስት ዴዔታ ሰለሞን ሶካ በበኩላቸው ፥ የሀገር ብልጽግና ያለ ሥራ ስለማይታሰብ ሌሊትና ቀን በመስራት የራዕያችን መዳረሻ ማድረስ ያስፈልጋል ብለዋል ።
መንግስት በሚያመቻችላቸው ገበያ ትስስር ብቻ ሳይወሰኑ የዓለም አቀፍ ገበያን በራሳቸው ጥረት እንዲቀላቀሉም ነው ያሳሰቡት ።
የክልሉ ሥራ ክህሎትና ኢንተርፕራይዞች ቢሮ ሃላፊ ሀገረጽዮን አበበ ፥ ሲዳማ ክልል ሆኖ ከተደራጀ ወዲህ ለወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር በተሰራው ሥራ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
በ2016 ዓ.ም ብቻ 260 ሚሊየን ብር ለኢንተርፕራይዞች ማሰራጨት መቻሉንና 800 ሄክታር መሬት መመቻቸቱንም ነው የተናገሩት። ለተከታታይ አምስት ቀናት በሚቆየው ባዛር በክልሉ በሁሉም ዞኖች የሚገኙ ከ200 በላይ ኢንተርፕራይዞች መሳተፋቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል ።