Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የቱርኩ የመሐል ተከላካይ ዴሚራል የሁለት ጨዋታ እገዳ ተጣለበት

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቱርኩ የመሐል ተከላካይ ሜሪህ ዴሚራል ሀገሩ ቱርክ ከኦስትሪያ ጋር በነበረው ጨዋታ ግብ ካስቆጠረ በኋላ ባሳየው አወዛጋቢ የደስታ አገላለፅ ምልክት በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ሁለት ጨዋታ እንዲታገድ ተደርጓል፡፡

የ26 ዓመቱ ዴሚራል በአውሮፓ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ኦስትሪያ ላይ ጎል ካስቆጠረ በኋላ ደስታውን ለመግለፅ የተጠቀመበትን ምልክት የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ሲመረምር ቆይቷል፡፡

በማህበሩ ምርመራ መሰረትም ሜሪህ ዴሚራል የተጠቀመው የአጅ ጣት ምልክት ግራጫ ተኩላዎች ወይም ግሬይ ዎልቭስ በመባል የሚጠራውን የቱርክ ብሄራዊ ንቅናቄ ፓርቲን የሚወክል ምልክት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

በዚህም መሰረት ተከላካዩ በእግር ኳስ ስፖርት ነክ ያልሆነ መልዕክት በማስተላለፉ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የሁለት ጨዋታ እግድ ተጥሎበታል።

በዚህም ነገ ምሽት ቱርክ ከኔዘርላንድስ ጋር በምታደርገው ጨዋታ አይሰለፍም፡፡

የተጫዋቹን የደስታ አገላለፅ ምልክት ተከትሎ ቱርክ የጀርመን አምባሳደርን መጥራቷ የተገለፀ ሲሆን፤ የጀርመኑ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ፋዘር “የቱርክ ቀኝ ጽንፈኞች በእኛ ስታዲየም ውስጥ ቦታ የላቸውም” ሲሉ ድርጊቱን አውግዘዋል፡፡

የተጨዋቹ ፖለቲካዊ መልዕክት በቱርካውያን ፖለቲከኞች ዘንድ መነጋገሪያ መሆኑ ተገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን በበርሊን ተገኝተው ሀገራቸው የምታደርገውን የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ይከታተላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በተመሳሳይ እንግሊዛዊው አማካይ ጁድ ቤሊንግሐም ከስሎቫኪያ ጋር በነበረው ጨዋታ የእንግሊዝን የአቻነት ግብ ካስቆጠረ በኋላ በእጁ ባሳየው ያልተገባ ምልክት አንድ ጨዋታ እና 30 ሺህ ዩሮ የገንዘብ ቅጣት ተጥሎበታል፡፡

በቤሊንግሐም ላይ የተላለፈው ቅጣት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተፈፃሚ የሚሆን በመሆኑ ነገ ሀገሩ ከስዊዘርላንድ ጋር በምታደርገው የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ተሰልፎ እንደሚጫወት ተነግሯል፡፡

እንዲሁም የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ከስሎቫኪያ ጋር በነበረው ጨዋታ ደጋፊወቹ ግርግር በማስነሳታቸው እና ርችት ይዘው ወደ ስታዲየም በመግባታቸው በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የ11 ሺህ ዩሮ ቅጣት ተጥሎበታል፡፡

 

 

 

Exit mobile version