አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት እያሳዩት ያለውን በጎ ሚና አጠናክረው እንዲቀጥሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ፡፡
ኮሚሽኑ ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ያዘጋጀው የሥልጠናና የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ማህሙድ ድሪር÷ የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች የኮሚሽኑን ዓላማ ለማሳካት በጎ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ጠቅሰው÷ ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይ በሚከናወኑ የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች ላይ ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በሥልጠናና ውይይት መድረኩ የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ከኮሚሽኑ ከፍተኛ ባለሙያዎች ጋር ተገናኝተው የምክክር ሂደቱን በተመለከተ እየመከሩ መሆኑ ተገልጿል።
የመድረኩ ዓላማ የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ስለ ሀገራዊ ምክክሩ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡