የሀገር ውስጥ ዜና

አረንጓዴ አሻራ ኢትዮጵያ ለስነ ምህዳር መጠበቅ ቁርጠኝነቷን ያሳየችበት ነው – አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ

By Amele Demsew

July 05, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ለአካባቢ ስነ ምህዳር መጠበቅ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየችበት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ተናገሩ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ችግኝ በመትከል የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና የክረምት በጎ ፈቃድ አግልግሎት በይፋ ጀምረዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች፣ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች እና የሚኒስቴሩና የተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች ተገኝተዋል።

አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ በወቅቱ እንዳሉት÷ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ለአካባቢ ስነ-ምህዳር መጠበቅ ተግባራዊ ቁርጠኝነቷን በማሳየት ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኘችበት ነው፡፡

በዚህ ዓመት 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ተዘጋጅተናል፤ ሁላችንም በርብርብ ይህን ማሳካት አለብን ብለዋል፡፡

ከሀገር ውስጥ ባሻገር መርሐ-ግብሩን በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ ሚሲዮኖች አማካኝነት ተግባራዊ በማድረግ የአካባቢ ጥበቃ መልካም ተሞክሮን ለወዳጅ ሀገራት ማጋራት ተችሏል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ በአርባ ምንጭ ከተማ ችግኝ እንደሚተክሉና የአቅመ ደካማ ዜጎችን ቤት በማደስ የአረንጓዴ አሻራና የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደሚያከናውኑም ተጠቁሟል።