Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በሰው ሰራሽ አስተውሎትና መሰል ቴክኖሎጂዎች ላይ ካልሰራን በምርት ተወዳዳሪ ሆኖ መቀጠል አይቻልም – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰው ሰራሽ አስተውሎትና መሰል ቴክኖሎጂዎች ላይ ካልሰራን በምርት ተወዳዳሪ ሆኖ መቀጠል አይቻልም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከም/ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ዓለም በአዳዲስ ፈጠረና ቴክኖሎጂ ዘርፎች በማይገመት ፍጥነት እየተለወጠ መሆኑን በመግለጽ ስለ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ወጥ እሳቤ ይዘን መስራትና መከተል ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

ለዚህም በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በኮኔክቲቪቲ፣ በባዮ ምህንድስና፣ በስፔስ ቴክኖሎጂ እና መሰል የዘመን ስልጣኔ በፍጥነት እየተራመደ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።

በዚህ ፍጥነት ለመራመድም በዘመኑ ቴክሎኖጂዎች ሽግግር ላይ መስራት ይገባል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የሮቦቲክስ ቴክኖሎጂ ልማዳዊ የሰው ልጅ አካሄዶችን ሙሉ በሙሉ በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እየተኩ መሆኑን ጠቅሰው÷ ይህን ስጋት ተገንዝቦ ወደ ተግባር መግባት ይገባል ብለዋል፡፡

ዘመኑን በዋጁ የሰው ሰራሽ አስተውሎትና መሰል ቴክኖሎጂዎች ላይ ካልተሰራ በምርት ተወዳዳሪ ሆኖ መቀጠል እንደማይቻልም አንስተዋል፡፡

በሰው ሰራሽ አስተውሎትና መሰል የዘመኑ ቴክኖሎጂዎች ላይ ልጆች መሰረታዊ ዕውቅት እንዲይዙ ነገን ማየትና በቴክኖሎጂ ላይ ወጥ እሳቤ ይዞ መከተል እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል፡፡

Exit mobile version