አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ጎረቤት ተኮር የጋራ ልማትና እድገት ትፈልጋለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።
በዚህም በዲፕሎማሲ ጉዳይ ላይ ባነሱት ሃሳብ እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ ጎረቤት ተኮር የጋራ ልማትና እድገት ትፈልጋለች፡፡
የሱዳን ጉዳይ እኛ ኢትዮጵያውያን እንደራሳችን በመመልከትና አድሎኣዊ ባልሆነ ፍትሃዊ መንገድ ሚናችንን መወጣት አለብን ብለዋል፡፡
ምክንያቱን ሲያነሱም አብዛኛው ግጭት ያለው በሚታረሱና በሚለሙ አካባቢዎች እንደሆኑም ነው ያነሱት፡፡
ኢትዮጵያ ጎረቤት ተኮር መሆኗን ለመገንዘብ ይረዳ ዘንድ ባነሱት መረጃ፥ ከህወሓት ጋር በነበረው ግጭት የሱዳን መንግስት ያለአግባብ አለመግባባት የገባንበትን ቦታ ይዞ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ሱዳን በተቸገረችበት ወቅት ቦታውን ለማስመለስ አልሞከረችም፤ ችግሮቻቸውን እስኪፈቱ እየጠበቅን ነው ብለዋል፡፡
በሰላሙ ጊዜም ለሱዳን ኤሌክትሪክ ኃይል ስንልክ ነበር በማለት ጠቅሰው፥ ሆኖም ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የሀገሪቱ መንግስት መክፈል ስላልቻለ ብለን መላክን አላቆምንም ነው ያሉት፡፡
ስለዚህም ኢትዮጵያ ጉርብትና በሰላም ጊዜ ብቻ ሣይሆን በችግር ጊዜ ነው ብላ እንደምታምን ማስረጃ እንደሆነም ነው ጠቅሰዋል፡፡
ሶማሊያን በሚመለከትም ለሶማሊያ ሰላምና አንድነት ሞተናል ሲሉ ገልጸው፤ ከማንም ሀገረ መንግስት በላይ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ያላትን ክብር ማሳየቷን ገልጸዋል።
በሶማሊያ አንድነት ጥያቄ ፈጥረን ሳይሆን ሁሉንም ጎረቤቶቻችን ጠይቀን ምላሽ በማጣታችን ነው ምላሽ ከሰጠን ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረምነው ብለዋል፡፡
የሶማሊያ መንግስት ይህን ጉዳይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ከመወያየት ይልቅ መክሰስን መምረጡ አስፈላጊ እንዳልሆነ አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ሶማሊያ እንድትበተን ቢፈልግ ልጆቹን ልኮ አይሞትም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጥያቄ የባህር በር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ እንልማ ነው ያልነው ብለዋል፡፡
በመሰረት አወቀ