Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አቶ አሻድሊ ሀሰን የክልሉን የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር  አስጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር  አሻድሊ ሀሰን በአሶሳ ዞን ባምባሲ ወረዳ ክልል አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብርን  አስጀምረዋል፡፡

አቶ አሻድሊ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት÷ መንግስት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ኢንሸቲቮችን ቀርፆ እያከናወነ ከሚገኘው ተግባራት መካከል አንዱ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር  ነው ብለዋል።

በዚህም በክልሉ ባለፉት ጊዜያት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በተከናወኑት ተግባራት ተጨባጭ ለውጦቶች መታየታቸውን አንስተዋል።

በዘንድሮው  የአረንጓዴ አሻራ መረሐ ግብር በክልሉ ከ70 ሚሊየን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቄሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን እና በአንድ ጀምበር 15 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል መታቀዱን ጠቅሰዋል።

ችግኞችን መትከል ብቻ ግብ  አይደለም ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ÷ችግኞችን  ከእንስሳት እና ከሰው ንኪኪ ነፃ በማድረግ  የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ፣የውሃ ሀብትን ለማሳደግ እና  የደን ሽፋን መጨመር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ የተገኘውን የመተባበር እና የአንድነት ተሞክሮም በሌሎች የልማት ስራዎችም መድገም እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version