አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመምህራንን ሕይወት ለማሻሻል መንግስት ተጨማሪ እርምጃዎችን ይወስዳል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከም/ቤቱ አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ እየሰጡ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመምህራንን ደመወዝ አስመልክተው እንዳሉት ፥ መምህራን ለኢትዮጵያ ደማቸውን ከመስጠትና ነገ በልጆቻችን እናየዋለን ከሚል ተስፋ ውጪ በቂ ነገር አግኝተው አያውቁም፡፡
በዚህም የመምህራንን ሕይወት ለማሻሻል መንግስት ተጨማሪ እርምጃዎችን ይወስዳል ነው ያሉት፡፡
ይሁን እንጂ በአንዳድ ክልሎች እያጋጠመው ያለው ችግር በአቅም ልክና በሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም መሰረት የማድረግ እንደሆነ ጠቅሰው ፥ ይህንን ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡
ያም ሆኖ የፌዴራል መንግስት ችግሩ እንዳይባባስ በብድር ለማገዝ ሙከራ ማድረጉን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስገነዘቡት፡፡
የክልል ምክር ቤቶች በጀታቸውን ሲያጸድቁ እነዚህን ጉዳዮች አይተው እና ተቆጣጥረው መገምገም እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
በመሰረት አወቀ