የሀገር ውስጥ ዜና

የሌማት ትሩፋት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ እያመጣ ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

By Feven Bishaw

July 04, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሌማት ትሩፋት ከተጀመረ ሁለት አመት እንኳ ያልሞላው ቢሆንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከም/ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ እየሰጡ ነው፡፡

በምላሻቸው የሌማት ትሩፋት ከተጀመረ ሁለት አመት እንኳ ያልሞላው ቢሆንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለአብነትም በዶሮ እርባታ የተሰሩ ስራዎች የእንቁላል ዋጋ እንዲቀንስ ማድረጉን ተናግረዋል

የማር ምርትን በተመለከተም ከለውጡ በኋላ ባለፉት ሶስት ዓመት በዓመት 30 ሺህ ቀፎ እንደነበር አስታውሰው፤ ዘንድሮ 1 ሚሊየን ቀፎ መድረሱን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የማር ምርት ከ7 እጥፍ በላይ ማደጉንም ነው በማብራሪያቸው የገለጹት፤ እነዚህ ምርቶች እያደጉ ሲሄዱ ደረጃ በደረጃ ዋጋ እየቀነሰ ይሄዳልም ነው ያሉት፡፡

መንግስት የተለያዩ ድጎማዎችን እያደረገ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትን እየደጎመ መሆኑን ገልጸዋል።

ምርታማነት እንዲያድግ ተጨማሪ ስራ መስራት አለብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የበጋ እርሻ ባለፈው ዓመት አስደማሚ ውጤት ነው ያመጣው፤ ዘንድሮም 24 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለማረስ እቅድ ተይዟል ብለዋል፡፡

በማር፣ በቡና፣ በስንዴና በእንስሳት ልማት፣ በሩዝ፣ በፍራፍሬና በሻይ በሚቀጥሉት 2 አመታት በምንሰራቸው ስራዎች ቀዳሚ ቦታ መያዝ እንችላለን ብለዋል፡፡

በፌቨን ቢሻው