አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አረንጓዴ አሻራ ለዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ትግል የተግባር ተምሳሌት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ÷የሀገሪቱን የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች በተለይም የኢትዮጵያን አረንጓዴ ዲፕሎማሲ ውጤት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው÷ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በተገበረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአካባቢ መራቆትን እና የደን ጭፍጨፋን በመዋጋት ረገድ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ብሎም ለዓለምአቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ትግል አርአያ መሆኗን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ችግኞችን ለጎረቤት ሀገራት በመስጠትም በቀጠናው በተለዋዋጭ የአየር ሁኔታ ምክንያት በተደጋጋሚ የሚደርሱ አደጋዎችን ለመከላከልና ለመዋጋት በሚደረገው ትግል ግንባር ቀደም ሆናለች ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ የቀጠናዊ ውህደት እንቅስቃሴ አካል እንዲሆን መሰራቱን የገለፁት ቃል አቀባዩ÷ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የምትጋራቸው ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ደህንነት እንዲጠበቅ የአረንጓዴ አሻራ ተደማሪ እሴት መጨመሩንም ገልጸዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ከጉባዔዎችና ተከታታይ ኮንፈረንሶች ባለፈ ተጨባጭ ስራ እንደሚያስፈልግ ለዓለም ማሳየቱንም መጥቀሳቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ ስራም ከ200 በላይ በሆኑ ሀገራት በመልካም ተሞክሮነት መወሰዱ ለዚህ ማሳያ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡