አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 42 ሆስፒታሎች የአገልግሎት ደረጃቸው እየተሻሻለ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለፁ፡፡
የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችና መፍትሄዎች ላይ ያተኮረ መድረክ ሚኒስትሯ በተገኙበት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተካሂዷል፡፡
በዚሁ ወቅት ዶክተር መቅደስ÷የዲላ ሆስፒታል የአገልግሎት መሻሻል ለሌሎች የጤና ተቋማት ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡
የዲላ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከሁለት አመታት በፊት ለአገልግሎት ምቹ እንዳልነበር አስታውሰው÷ተቋማቸው ከዲላ ዩኒቨርሲቲና ከዞኑ ጋር በመተባበር ባደረገው ርብርብ አገልግሎቱ መሻሻሉን ተናግረዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ የጤና ተቋማትን አገልግሎት ማሻሻል ትኩረት እንደተሰጠው በመግለጽ በሀገር አቀፍ ደረጃ የባለሙያ ስልጠና እና የሆስፒታሎችን ፅዳትና አቀማመጥ መለወጥ ላይም እየተሰራን ነው ብለዋል።
በጥላሁን ይልማ