የሀገር ውስጥ ዜና

ተመድ በግጭት ለተጎዱ ሴቶች የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ ገለጸ

By Melaku Gedif

July 03, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) በኢትዮጵያ ከግጭት ጋር በተያያዘ ጉዳት ለደረሰባቸው ሴቶች የሰብዓዊ ድጋፍ በአግባቡ ተደራሽ እንዲሆን የክትትል ሥራዎችን በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ከተመድ ዋና ጸሐፊ የሥርዓተ ጾታ ጉዳይ ሃላፊ ክርስቲያን ኤፍ ሰንደርስ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)÷ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችንና ትንኮሳዎችን ለመከላከል፣ የሥርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥና ሴቶችን ለማብቃት በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡

በተለይ ያለዕድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ መስራት በመቻሉ አበረታች ውጤት መምጣቱን ገልጸዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሽልማት መብቃቷንና ለተገኘው ስኬትም የዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበር አንስተዋል፡፡

በተለያየ ጊዜ በግጭትና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶች ለመደገፍና ለማቋቋም መንግስት ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የተጀመሩ ሥራዎችን ለማስቀጠል የዓለም አቀፍ ተቋማት የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ጥሪ ማቅረባቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ክርስቲያን ኤፍ ሰንደርስ በበኩላቸው÷ ሴቶችን ከጥቃት ለመከላከልና መብታቸውን ለማስከበር እንዲሁም ከግጭት ጋር በተያያዘ ጉዳት ለደረሰባቸው ሴቶች የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ በአግባቡ ተደራሽ እንዲሆን በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ተመድ የክትትል ሥራዎችን በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ነው የገለጹት፡፡

በቀጣይም ሚኒስቴሩ ለሚሰራቸው ሥራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ሃላፊው አስታውቀዋል።