የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያና ጃፓን በተለያዩ የጤና ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት ተስማሙ

By Amele Demsew

July 02, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ጃፓን በኢትዮጵያ እየተተገበረ የሚገኘውን ጠንካራ የጤና ስርዓት ግንባታ በማጠናከርና በሌሎች የጤና ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት መስማማታቸው ተጠቆመ፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳቫ ከጃፓን የህዝብ ተወካዮች አባላት ልዑካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም ዶክተር መቅደስ ዳባ ጃፓን የሀገራችንን የጤና ዘርፍ ለመደገፍ ላሳየችው ፍላጎት አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና ጃፓን ለዘመናት የቆየ አጋርነት እንዳላቸውም ሚኒስትሯ አንስተዋል።

የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ በጤናው ዘርፍ በግሎባል ፈንድ እና ጋቪ አማካኝነት በሚያደርገው ድጋፍ በርካታ የጤና ኢኒሼቲቮች ትግበራ ሂደት ዉስጥ ጉልህ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተጠቅሷል ፡፡

በውይይቱም ሁለቱ ወገኖች በኢትዮጵያ እየተተገበረ የሚገኘውን ጠንካራ የጤና ስርዓት ግንባታ በማጠናከርና በሌሎች የጤና ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት መስማማታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የሀገር ዉስጥ የህክምና ግብዓቶች ምርትን ለማሳደግ፣ የጤና ዘርፍ ፋይናንስ፣ የዲጂታል መረጃ አያያዝና ሌሎች የጤና ጉዳዮች ላይም ጃፓን ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንደምትሰራ የልዑካን ቡድኑ አባላት ገልጸዋል፡፡