አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በየደረጃው የተካሄዱ ሕዝባዊ ኮንፈረንሶች የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ ምቹ መደላድል መፍጠራቸውን የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡
በጸጥታው ዘርፍ የተከናወኑ የ100 ቀናት የሰላም ማስፈን ስራዎችን የገመገመ መድረክ በጎንደር ከተማ ተካሂዷል፡፡
የመድረኩ ዓላማ በክልሉ የተከናወኑ የሰላምና የሕግ ማስከበር ተግባራትን በመገምገም በዘርፉ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ለማጠናከር መሆኑን የቢሮው ምክትል ኃላፊ ኮማንደር ደጀኔ ልመንህ አስገንዝበዋል፡፡
የተካሄዱ ኮንፈረንሶችም በርካታ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪውን ተቀብለው በመግባት ወደ ሕብረተሰቡ ተቀላቅለው ሰላማዊ ሕይወት እንዲመሩ አስችለዋል ብለዋል፡፡
የተገኘው ሰላም ለልማት ስራዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን በመግለጽ በቀጣይም በሰላምና ልማት የላቀ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰራ ማመላከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የሰሜን ጎንደር ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ ዳኝነት ንጉሴ በበኩላቸው÷ የመጣው ለውጥ የመንግሥት ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤ ሕዝቡም የመንግሥትን አገልግሎት እንዲያገኝ አስችሏል ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡
በዞኑ ዘላቂ ሰላምን በማረጋጋጥ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው እንደሚሠራም ጠቅሰዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ከጎንደር ከተማ፣ ከሰሜን ጎንደር፣ ከማዕከላዊ ጎንደር እና ከምዕራብ ጎንደር ዞኖች የተውጣጡ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊዎችና የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራር አባላት ተሳትፈዋል፡፡