የሀገር ውስጥ ዜና

ረቂቅ ህጎች ሲዘጋጁ ዜጎች እንዲሳተፉ ማስቻል አስተዋጽዖው ከፍተኛ እንደሆነ ተጠቆመ

By Meseret Awoke

July 02, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በፍትህ ሚኒስቴር የሚዘጋጁ ረቂቅ ህጎች ላይ ዜጎች ሃሳብ በመስጠት እንዲሳተፉ ማስቻል አስተዋጽዖው ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የፍትህ ሚኒስቴር በህግ ረቂቅ ላይ የባለድርሻ አካላትን የበለጠ ለማሳተፍ ያስችላል ያለውን አዲስ የምክክር ማኑዋል እና በበይነ መረብ ምክክር ለማድረግ የሚያስችል ድረ-ገፅ ይፋ ማድረጉን አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ ከዚህ በፊት ወጥነት ያልነበረውን የህዝብ ተሳትፎ አሰራርን የሚቃኝ የአሰራር ማኑዋል አዘጋጅቶ ያስመረቀ ሲሆን፥ ተሳትፎውን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ የኮንሰልቴሽን ፖርታል አብሮ ይፋ አድርጓል።

የምክክር ማኑዋሉ እና ፖርታሉ በህግ ማርቀቅ ሂደት ውስጥ የተሻለ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት እንዲኖር ከማስቻሉም ባሻገር በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ያሉ ዜጎች አስተያየት በመስጠት ሂደት ውስጥ እንዲሳተፉ በማድረግ የተሻሉ ህጎች እንዲረቁ ያግዛል ነው የተባለው።

ከዚህ ቀደም ለምክክር የሚውሉ ወጪዎችንም ያስቀራል መባሉን ፍትህ ሚኒስቴር ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከላከው መረጃ ማወቅ ተችሏል፡፡

በበይነ መረብ የሚደረገውን ምክክር ድረ-ገፅ በጋራ ለማስተዳደርና ቀጣይ ስልጠናዎችን ለመስጠት የፍትህ ሚኒቴር እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።