አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም፤ በአውሮፓ ህብረትና በአካባቢው ማህበረሰብ ትብብር በስልጤ ዞን ዳሎቻ ከተማ እየተገነባ ያለው የውሃ ፕሮጀክት ከንጹህ መጠጥ ውሃ ባለፈ የአርሶ አደሩን የግብርና ስራዎች በሚያግዝበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።
በክልሉ በንጹህ መጠጥ ውሃና በግብርና ዘርፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማካሄድ የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ ተወካይ ጌታመሳይ ደመቀ እና የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ዘይቱና ኢብራሂም በወቅቱ ተፈራርመዋል።
ፕሮጀክቱ ሶስት ወረዳዎች በንጹህ መጠጥ ውሃ እንዲሁም 17 ወረዳዎች ደግሞ በግብርና ፕሮጀክቱ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚተገበረው ይህ ፕሮጀክት፤ 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ዩሮ በጀት እንደተያዘለት መገለጹን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡