Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ቦርዱ የቀሪና ድጋሚ ምርጫ ጊዜያዊ ውጤቶችን እያረጋገጠ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቀሪና ድጋሚ ምርጫ በተካሄደባቸው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፣ አፋር፣ ሶማሌ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች በጊዜያዊነትይፋ የተደረጉ የምርጫ ውጤቶችን እያረጋገጠ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡

የቦርዱ የምርጫ ኦፕሬሽን ክፍል ሃላፊ ብሩክ ወንድወሰን÷በማዕከላቱ በጊዜያዊነት ይፋ የተደረጉ ውጤቶችን ከየምርጫ ክልሉ ወደ ማረጋጫ ማዕከል በመቀበል የማረጋገጥ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በማዕከሉ በምርጫ ጣቢያዎች የተገኙ ውጤቶችን ከእያንዳንዱ የምርጫ ክልል አስፈጻሚዎች ፊት ለፊት በመረከብ የማጣራት ሥራ መጀመሩን ጠቅሰዋል።

የተመዘገበ የመራጭ ቁጥር፣ ድምጽ የሰጠ፣ ዋጋ አልባ እና የድምር ትክክለኛነት በማዕከሉ የማጣራት ሥራ የሚደረግባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሚቀጥሉት ቀናት የማንዱራና ወንበራ ምርጫ ክልሎች የምርጫ ውጤቶች ለማዕከሉ ቀርበው ሲረጋገጡ የምርጫው አጠቃላይ ውጤት ይፋ እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡

በታሪኩ ወ/ሰንበት

Exit mobile version