የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሠላም መረጋገጥ ከፍተኛ አሥተዎፅኦ እያበረከተች ነው

By ዮሐንስ ደርበው

July 01, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሠላም መረጋገጥ ከፍተኛ አሥተዎፅኦ እያበረከተች መሆኗ ተገለጸ፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ልዑክ በኢትዮጵያ ወታደራዊ ዝግጁነት ዙሪያ የጋራ ምክክር እያካሄደ ነው፡፡

በመድረኩም የተጠንቀቅ ኃይሉን ሁለንተናዊ የግዳጅ አፈፃፀም የተመለከተ የዳሰሳ ጽሑፍ መቅረቡን የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ አመላክቷል፡፡

በቀረበው ጽሑፍም ኢትዮጵያን ጨምሮ አባል ሀገራቱ የቀጣናውን ሠላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ መሆኑ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ የተጠንቀቅ ኃይሉ መሥራች እንደ መሆኗ የተቋሙን ራዕይ ለማሳካት ወሳኝ ሚና መጫወቷንም የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪና የተኩስ አመራር ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አለምሸት ደግፌ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጦር በትጥቅና በሰው ኃይል እንዲሁም በከፍተኛ ተነሳሽነት የቀጣናውን ሠላም ለማረጋገጥ በሙሉ ዝግጁነት ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ዋና ዳይሬክተር ብርጋዲየር ጄኔራል ፓውል ጀማ በበኩላቸው በቀጣናው በሚካሄዱ ወታደራዊ ኦፕሬሽኖች ኢትዮጵያ ያላትን ተሳትፎ አድንቀው÷ ዝግጁነትን በማረጋገጥ በቀጣይም በቅንጅት እንሠራለን ብለዋል።

የምሥራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ቡድን እያደረገ ያለው የዝግጁነት ፍተሻ ዝግጁነታችንን የሚያረጋግጥ ነው ያሉት ደግሞ የተጠንቀቅ ኃይሉ የኃይል አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ጌታቸው አሊ ናቸው፡፡

በቀጠይ ለምናደርገው የግዳጅ አፈፃፀምም ትልቅ እገዛ ያደርጋል ብለዋል፡፡

በምሥራቅ ቀጣና ያለውን የሽብርተኝነት፣ የአክራሪነትና የተለያዩ ግጭቶችን ለማስቆም የተጠንቀቅ ብርጌድ በአስተማማኝ ዝግጁነት ላይ መሆኑ በቀረቡ ሪፖርቶች ተመላክቷል፡፡

በነገው ዕለትም የተጠንቀቅ ሻለቆች ሁለንተናዊ ቁመና ይፈተሻል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተመላክቷል፡፡