አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከጋናውያን ቤተሰቦች የተወለደው ኒኮ ዊሊያምስ እንዲሁም ከኢኳቶሪያል ጊኒ እና ሞሮኮ የዘር ግንድ ካላቸው ቤተሰቦች የተገኘው ላሚን ያማል በአውሮፓ ዋንጫ ከስፔን ብሄራዊ ቡድን ጋር ድንቅ ጊዜን እያሳለፉ ይገኛሉ፡፡
በትናንት ምሽት ስፔን ጆርጂያን 4 ለ 1 በሆነ ሰፊ የጎል ልዩነት ባሸነፈችበት ጨዋታ ኒኮ ዊሊያምስ አንድ ጎል ሲያስቆጥር፤ አንድ ለጎል የሚሆን ኳስ አመቻችቶ አቀብሏል።
ኒኮ የትናንትናውን ጨዋታ ተከትሎ በአንድ ጨዋታ ጎል ያስቆጠረ፣ አመቻችቶ ያቀበለ፣ እንዲሁም መቶ በመቶ የተሳኩ ቅብብሎችን ያደረገ የመጀመሪያው ተጫዋች በመሆን አዲስ ክብረ ወሰን አስመዝግቧል፡፡
የ22 ዓመቱ የፊት ተመላላሽ መስመር ተጨዋች ኒኮ ዊሊያምስ በህገ ወጥ መንገድ ፈልሰው ወደ ስፔን ከመጡ ጋናውያን ቤተሰቦች የተገኘ መሆኑን ነው ተጫዋቹ ባደረገው ቃለ ምልልስ ተናግሯል፡፡
የኒኮ ዊሊያምስ ቤተሰቦች ከረጅም የስደት ጉዞ በኋላ ከአፍሪካ ሰሜናዊ ክፍል በምትዋሰነው እና ሜሊላ በምትባለው የስፔን ግዛት ታስረው እንደነበር እና ወላጆቹ በስደት አስከፊ ጊዜን ማሳላፋቸውን እንደገለጸ ቢቢሲ ስፖርት አስነብቧል፡፡
አባቴ እግሩ ላይ ጠባሳ አለበት፣ እስከ 18 ዓመቴ ድረስ ለምን እንደሆነ አላውቅም ነበር፣ ነግር ግን ለአትሌቲኮ ቢልባኦ መጫወት እደጀመርኩ እናቴ የጠባሳውን ታሪክ አጫወተችኝ።
አባቴ በህገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት እጅግ ፈታኝ በሆነው የሰሃራ በረሀ አቋርጦ አውሮፓ ለመግባት ባደረገው ጉዞ ነው የበረሃው ንዳድ ቃጥሎ ለጠባሳ የዳረገው ብሏል።
በስፔን የጥገኘነት ፈቃድ ለማግኘትም ቤተሰቦቹ ከጋና መጥተው ሳለ በወቅቱ ጦርነት ከተከሰተባት ላይቤሪያ እንደመጡ በማስመሰል የጥገኝነት ፈቃድ ማግኘታቸውንም ይገልፃል፡፡
በቆዳ ቀለሙ እና በአፍሪካዊነቱ ምክንያት በተደጋጋሚ የዘረኝነት ጥቃት ሰለባ እንደሆነ የሚናገረው ኒኮ ዊሊያምስ ከብሔራዊ ቡድን በተጨማሪ በስፔኑ አትሌቲኮ ቢልባኦ ከወንድሙ ኢናኪ ዊሊያምስ ጋር ድንቅ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል፡፡
ታናሽ ወንድሙ ኢናኪ ዊሊያምስ ለጋና ለመጫዎት ሲመርጥ ለስፔን ብሄራዊ ቡድን መጫዎትን የመረጠው ኒኮ በአውሮፓ ዋንጫው የዋንጫ ግምት በተሰጠው የስፔን ብሄራዊ ቡድን አይተኬ ግልጋሎቱን እየሰጠ ይገኛል፡፡
ሌላኛው አፍሪካዊ ላሚን ያማል ከአፍሪካውያን ቤተሰቦች የተገኘ ነገር ግን በወረቀት የስፔን ዜግነት ያለው ወጣት ባለ ተሰጥኦ አጥቂ ነው፡፡
የበርካታ ክብረ ወሰኖች ባለቤት መሆን የቻለው የ16 ዓመት ከ11 ወራት ዕድሜ ያለው አጥቂ የስፔን ብሔራዊ ቡድን ወሳኝ ተጫዋች ነው፡፡
በትናንት ምሽቱ ጨዋታ ለጎል የሚሆን ኳስ አመቻችቶ ማቀበል የቻለው ያማል የፖላንዳዊውን ካሰፐር ኮዞልስኪ ክብረ ወሰን በአንድ ዓመት በማሻሻል የአውሮፓ ዋንጫ ትንሹ ተጫዋች መባሉ ይታወሳል።