ቴክ

በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ከቻይና ብሄራዊ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ሃላፊዎች ጋር ተወያዩ

By Shambel Mihret

July 01, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ከቻይና ብሄራዊ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ሃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

ውይይቱ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ አላማ ለመጠቀም ባሉ አማራጮች ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል፡፡

በዚሁ ወቅት በለጠ ሞላ (ዶ/ር)÷ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን በጤና፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በሃይል አማራጭ ዙርያ ለሰላማዊ አላማ ለመጠቀም ከሩሲያ ፌደሬሽን ሮሳተም ኮርፖሬሽን ጋር እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በዘርፉ ውጤታማ ስራ ለመስራት የኒውክሌር ኢነርጂ አቅም ግንባታ ዘርፎች ላይ የሰው ሃብት ልማት ስልጠና ላይ ሚኒስቴሩ ከቻይናው ኑክሌር ኮርፖሬሽን ጋርም አብሮ ለመስራት ፍላጎት እንዳለው አስረድተዋል።

የቻይናው ብሄራዊ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ተወካዮች በበኩላቸው÷ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የኒውክሌር ልህቀት ማዕከል አቅም ግንባታ ላይ እገዛ ለማድረግ ስምምነት ለመፈረም የመጀመሪያ ዙር ውይይት ማደረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡

በዚህም በኢትዮጵያ የሰው ሃብት ስልጠና እና ሌሎችም የዘርፉ ስራዎች ላይ መስራት እንደሚፈልጉ ገልጸው በስራው አተገባበር ዙሪያ ውይይቶች እንደሚካሄዱም መገለጹን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡