አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፊፋን እና የካፍን ደረጃ የጠበቀ ስታዲየምና የሕዝብ በዓላት ማክበሪያ በአርባምንጭ ከተማ ሊገነባ ነው።
“ሲሲሲሲ” የተሰኘው የቻይና ተቋራጭ እና “ስታድያ’ የምህንድስና ሥራዎች አማካሪ አክሲዮን ከአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ጋር የአርባምንጭ ሁለገብ ስታዲየም የግንባታ ውል ተፈራረመዋል።
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባይነህ አበራ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ዞኑ በርካታ ስፖርተኞችን ያፈራ የኳስና የሸማ ጥበብ መፍለቂያ ሆኖ ሳለ ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም አለመኖሩ ቁጭት ፈጥሯል።
የሚገነባው ስታዲየም ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ጨዋታዎችን የሚያስተናገድ የፊፋን እና የካፍን ስታንዳርድ የሚያሟላ እንደሚሆንና ከ1 ቢሊየን ብር በሚበልጥ ወጪ እንደሚገነባ ተናግረዋል፡፡
ግንባታው ከ2 ሚሊየን በሚበልጠው የጋሞ ዞን ሕዝብ እና መንግስት ትብብር እንደሚገነባ መግለጻቸውንም የጋሞ ዞን ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ በበኩላቸው÷የስታዲየሙ መገንባት በዞኑ ስፖርት ዘርፍ ተጨማሪ የቱሪዝም ፍሰትን የሚጨምር፤ የቱሪዝም ገቢንም የሚያሳድግ ነው ብለዋል።