የሀገር ውስጥ ዜና

በክልሉ ለ64 ሺህ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩ ተገለጸ

By Amele Demsew

June 30, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በበጀት ዓመቱ ከ64 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩን የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ሃላፊ ግዛው ጋግያብ እንደገለጹት ÷በ2016 በጀት ዓመት በከተማና በገጠር በተደረገ እንቅስቃሴ 64 ሺህ 136 ዜጎችን በቋሚ የሥራ ዕድል አግኝተዋል።

ክልሉ ባለው ፀጋ ሥራ ፈላጊ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲቻል ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።

በተለይ ወጣቶች በተለያዩ የግብርና መስኮች ተሰማርተው ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል በተደረገ ጥረት በርካቶች ወደስራ መግባታቸውንና የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ውስጥ 33 ሺህ የሚሆኑት በዚሁ ዘርፍ የተሰማሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ቢሮው ለወጣቶቹ የመስሪያ ቦታና የሥራ መጀመሪያ ካፒታል ማመቻቸቱን የገለጹት ሃላፊው÷ በበጀት ዓመቱ ወደ ሥራ ለገቡ ወጣቶች ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ብድር ተሰጥቷል ብለዋል።

በተጨማሪም ለመስሪያና መሸጫ ቦታ የሚሆን ከ6 ሺህ 293 ሄክታር በላይ መሬትና 141 ሼዶች ተገንብተው ለወጣቶች እንደተላለፉ መገለጹንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡