አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የክልል የመዋቅር ጥያቄዎች ሰላማዊ፣ የሕዝቦችን አብሮነት እና ወንድማማችነት ሊያጠናክር በሚችል መልኩ በሕዝበ ውሳኔ ምላሽ መሠጠቱ ለምክር ቤቱ ይቀርቡ የነበሩ ተደጋጋሚ አቤቱታዎችና ቅሬታዎች ማስቀረት እንደቻለ ገለጹ፡፡
የማንነት ያስተዳደር ወሰንና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ አቶ ፍቅሬ አማን የቋሚ ኮሚቴውን የ2016 በጀት ዓመት ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴ አባላት አቅርበዋል፡፡
በዚህም በበጀት ዓመቱ ከተፈጸሙት አንኳር ተግባራት መካከል አንዱ ክልሎች ያቀርቧቸው የነበሩትን ተደጋጋሚ የመዋቅር ጥያቄዎች የሕዝቡን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ምላሽ መሰጠቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱና ግጭቶች እንዲወገዱ አስችሏል ብለዋል፡፡
ፀሐፊው አያይዘውም የግጭት መከላከል ስትራቴጂክ እቅድ ተጠንቶ ወደተግባር እንዲገባና ክልሎች እንዲጠቀሙበት ርክክብ መደረጉ በክልሎች መካከል የሚነሱ ግጭቶች ለመከላከል እንደሚያስችልም ነው ያስታወሱት፡፡
ከማንነትና ከአስተዳደር ወሰን ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ አቤቱታዎችን ምላሽ ለመስጠት የመከታተልና የመደገፍ ሥራ የተሠራ ቢሆንም በክልሎች መካከል ተንቀሳቅሶ ጥናት ለማድረግ በአካባቢው ያለው የፀጥታ ችግር እንቅፋት እንደሆነባቸው ጠቅሰዋል፡፡
የማንነት ያስተዳደር ወሰንና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጥላሁን ከበደ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትኖግራፊና የቋንቋ አትላስ (ፕሮፋይል) እንዲቀርብ በጠየቁት መሠረት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህልና ማኅበራዊ ጥናት ተማራማሪ ባይለየኝ ጣሰ(ዶ/ር) የፕሮጀክቱን መነሻ ሃሳብ አቅርበዋል ነው የተባለው፡፡
ምክር ቤቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትኖግራፊና የቋንቋ አትላስ (ፕሮፋይል) ጥናት ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እንደተሠሩ አስታውሰዋል፡፡
ጥናቱ ለሕግ አውጪዎችና ለሀገራዊ ፖሊሲ አመንጪዎች እንደግብዓትነት ለማገልገል፣ በተሳሳተ ግንዛቤ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን ለመቆጣጠርና በሕዝቦች መካከል ጠንካራ ትስስርና ሕብረብሔራዊ አንድነትን የሚጠናክርበትን አሠራር ለመዘርጋት የላቀ ፋይዳ እንዳለውም ነው ያብራሩት፡፡
በመጨረሻም ቋሚ ኮሚቴው ለዕለቱ በተያዙት አጀንዳዎች ላይ በመምከርና ለምክር ቤቱ በሚቀርቡ የውሳኔ ሃሳቦች ላይ ስምምነት ላይ በመድረስ ጉባኤውን ማጠናቀቁን በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል፡፡