አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደሴ ከተማ ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተሰሩ 33 የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ምርቃትና ጉብኝት እየተካሄደ ይገኛል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
የሕዝብን የልማት ጥያቄ መሠረት ያደረጉ የመንገድ፣ የመናኸሪያ፣ የቢሮ፣ የውሃ፣ የጤና፣ የትምህርት ቤት እና ሌሎች በርካታ ተቋማት ፕሮጀክቶች ናቸው እየተመረቁ የሚገኙት።
አብዛኞቹም ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች እንደሆኑም ነው የተገለፀው።
ከፕሮጀክቶቹ ውስጥ 87 ሚሊየን ብር የሚያወጡ ልማቶቾ በማህበረሰቡ የተሸፈኑ ናቸው ተብሏል።
የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን ምርቃ መርሐ ግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት ፥ በከተማው የታየው የልማት እንቅስቃሴ መንግስትና ማህበረሰቡ ሲደመር ያመጣው ውጤት ነው፡፡
የአከባቢው ማህበረሰብ አሁንም ያለውን ሰላም በማስቀጠል ልማቱን ማፍጠን ይገባዋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ ከ1ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ የወጣባቸው የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው ያሉት የከተማዋ ተቀዳሚ ም/ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው ፥ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በማከናወን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግና ከተማዋን ስማርት ሲቲ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በግንባታ ላይ ያሉና የተጠናቀቁ የአስፋልት መንገድ፣ መናኸሪያ፣ ጤና ጣቢያ፣ ትምህርት ቤት፣ መድኃኒት ቤት፣ የዳቦና የዱቄት ፋብሪካ፣ የወጣት ማዕከል እና ሌሎች በርካታ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም ነው ያብራሩት።
ዛሬ ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ የወጣባቸው የልማት ስራዎች መመረቃቸውን ያነሱት ከንቲባው ፥ ከ87 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆነው የማህበረሰብ ተሳትፎ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ማህበረሰቡ ለልማቱ እያደረገ ያለውን ድጋፍ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
በከድር መሀመድ