አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመከላከያ የሎጂስቲክስ ዋና መምሪያ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት በአርዓያነት የሚወሰዱ መሆናቸውን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ እና የሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች የዋና መምሪያውን የሥራ እንቅስቃሴ መጎብኘታቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ አመላክቷል፡፡
በጉብኝታቸውም በቆሬ አካባቢ የተገነባውን ዘመናዊ የመኪና ማከማቻና ጋራዥ፣ በቃሊቲ ገመኔ አካባቢ ያለውን የሎጂስቲክስ የትራንስፖርት ማዕከል እና በመልካ ቃሊቲ ያለውን የንብረት ማከማቻ ተመልክተዋል፡፡
በዚሁ ወቅትም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ባደረጉት ንግግር÷ ዋና መምሪያው የሠራዊቱን የውጊያ ድጋፍ በማገዝ፣ ዝግጁነቱን በማረጋገጥ፣ በአዲስ መልክ በአጭር ጊዜ ለሥራ የገነባቸው መሠረተ-ልማቶች፣ የታጠቃቸውን ንብረቶች በአግባቡ በመያዝ፣ የሥራ አካባቢን ንፁህና ሳቢ በማድረግ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት በአርዓያነት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል፡፡