አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መቻል የስፖርት ክለብ ከምስረታው ጀምሮ በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች ባስመዘገባቸው ድሎች፣ በነበሩ ተግዳሮቶችና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄደ፡፡
ክለቡ ከሰኔ ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ “መቻል ለኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሐሳብ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በማክበር ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የዛሬው ውይይትም የአከባበሩ አካል ሲሆን በመድረኩም÷ የሰራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሰራዊቱ የክብር አባላት፣ በክለቡ የነበሩ ስፖርተኞች፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ክለቡን በአስተዋፅኦው ልክ ለመዘከርና ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ክለቡ በተለያዩ ምክንያቶች ከገጠመው ፈተና ወጥቶ ውድድሮችን የሚያሸንፍ እና የተስተካከለ አቋም ያለው እንዲሆን ባለ ድርሻ አካላት በትጋት እንዲሠሩም አሳስበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የክለቡን ዝና ለመመለስ በተቋሙ የተሰጠውን ትኩረት ማድነቃቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ አመላክቷል፡፡