የሀገር ውስጥ ዜና

ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍልና በክልሎች የተመጣጠነ ዕድገት ማረጋገጥ ለጠንካራ የፌዴራል ስርዓት መሠረቶች ናቸው – አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

By Feven Bishaw

June 29, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል፣ ውጤታማ የፊስካል ሽግግር እና በክልሎች መካከል የተመጣጠነ ዕድገትን ማረጋገጥ ለጠንካራ የፌዴራል ስርዓት ጽኑ መሠረቶች ናቸው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ።

«የፊስካል ፌዴራሊዝም መሰረታዊ ጉዳዮች እና የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ» በሚል ርዕስ ለምክር ቤት አባላት ስልጠና እየተሰጠ ነው።

በስልጠና መድረኩ አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፤ ፌዴራላዊ ሥርዓት ከሌሎች ሥርዓተ መንግሥታት በተሻለ ደረጃ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ የሕዝቦችን በእኩልነት አብሮ የመኖርና በጋራ የመበልፀግ ዓላማ ለማሳካት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ለሥርዓቱ ዘላቂነት ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል፣ ውጤታማ የፊስካል ሽግግርና በክልሎች መካከል የተመጣጠነ እድገትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡

ያልተማከለ የፋይናንስ አስተዳደር በሚከተሉ ሀገራት ተግባራዊ ከሚደረጉ የፊስካል ሽግግሮች አንዱ የጋራ ገቢ ክፍፍል መሆኑን ጠቅሰዋል።

በክልሎች መካከል የተመጣጠነ ዕድገትን ለማረጋገጥና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚዘጋጁ ቀመሮችን፣ ምክረ ሃሳቦችን፣ የሕግ ማዕቀፎችንና የአሠራር ሥርዓቶችን ጥራት በማረጋገጥና ተግባራዊ እንዲሆኑ ምክር ቤቱ የማይተካ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል።

በመሆኑም የምክር ቤቱ አባላት በእውቀትና በመረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ለማሳለፍ የሚያስችል ስልጠና እንዲያገኙ ማድረግ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው መናገራቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የክልሎችና የፌዴራሉ መንግሥት የጋራ ተብለው የተመደቡ ገቢዎች በሁለቱ መካከል የሚከፋፈልበትንና የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች ድጎማ የሚሰጥበትን ቀመር እንደሚወስን ይታወቃል፡፡