አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ስፔናዊው ታዳጊ ላሚን ያማል በአውሮፓ ዋንጫ ታሪክ በእድሜ ትንሹ ተጫዋች ሆኖ ሲመዘገብ የፖርቹጋሉ ተከላካይ ፔፔ ደግሞ የምንጊዜም በእድሜ ትልቁ ተጫዋች ሆኖ ተመዝገቧል፡፡
የባርሴሎናው የክንፍ ተጫዋች ላሚን ያማል 16 ዓመት ከ11 ወር ላይ የሚገኝ ሲሆን÷ በፖላንዳዊው ካሰፐር ኮዞልስኪ ተይዞ የነበረውን ክብረ-ወሰን በአንድ ዓመት ማሻሻል ችሏል፡፡
ያማል በጀርመን አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኛው የአውሮፓ ዋንጫ ስፔን ከክሮሺያ ባደረገችው የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ በቋሚ 11 አሰላለፍ ውስጥ በመግባት መጫወቱ ይታወሳል፡፡
በጨዋታውም ለግብ የሚሆን ኳስ አመቻችቶ በማቀበል ሌላ ክብረ-ወሰን ማስመዝገቡ ነው የተገለጸው፡፡
ላሚን ያማል ቀደም ሲል በስፔን ላ ሊጋ፣ የስፔን የንጉስ ዋንጫ እና በስፔን ክለቦች የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ በእድሜው ትንሹ ግብ ያስቆጠረ የሚለውን ክብረ-ወሰን ማሻሻሉ የሚታወስ ነው፡፡
በሌላ በኩል የፖርቹጋሉ ተከላካይ ፔፔ በ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ በ41 ዓመቱ በመሰለፍ አዲስ ክብረ-ወሰን አስመዝግቧል፡፡
በሙሉ ስሙ ኬፕለር ላቬራን ሊማ ፌሬራ (ፔፔ) እየተባለ የሚጠራው አንጋፋው ተከላካይ በዘንድሮው አውሮፓ ዋንጫ ፖርቹጋል ካደረገቻቸው ሶስት የምድብ ጨዋታዎች ውስጥ በሁለቱ ተሰልፎ የተጫወተ ሲሆን÷ ከተጠበቀው በላይ ጥሩ አቋም በማሳየት ከእግር ኳስ ቤተሰቡ አድናቆት ተችሮታል፡፡
በመድረኩ በእድሜ ትልቁ ተጫዋች የሚለው ክብረ-ወሰን ከዚህ በፊት በሀንጋሪው ጋቦር ኪራሊ ተይዞ የነበረ ሲሆን÷ በ2016ቱ የፈረንሳይ የአውሮፓ ዋንጫ ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር ተሰልፎ መጫወት ችሏል፡፡
በተመሳሳይ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ በአማካይ እድሜ ትንሹ ብሄራዊ ቡድን የቼክ ሪፐብሊክ ብሔራዊ ቡድን ሲሆን÷ የተጫዋቾች አማካይ እድሜ ጣሪያ በአማካይ 25 ነጥብ 5 ነው፡፡
በእድሜ አንጋፋው ብሄራዊ ቡድን ደግሞ የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ሲሆን÷የተጫዋቾች አማካይ እድሜ 28 ነጥብ 5 ነው መባሉን ጌምስ ማርኬት አስነብቧል፡፡