አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና የኢትዮ-ጣልያን የወዳጅነት ልዑክ የዲፕሎማሲ ሥራን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር)÷የሁለቱ ሀገራት ህዝቡችን የጋራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትብብር እንደሚሰሩ አስረድተዋል፡፡
የጣልያን ባለሃብቶች ያላቸውን ልምድ እና ተሞክሮ ተጠቅመው በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሌላ በኩል በሀገሪቱ ያሉ አለመግባባቶች በተቋቋመው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በኩል ተለይተውና ተጠንተው የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የጣልያን የም/ቤት አባላትበበኩላቸው÷ ጣልያን ከኢትጵዮያ ጋር በኢኮኖሚው ዘርፍ በጋራ ተጠቃሚነትና የህዝብ ለህዝብ ወዳጅነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ መናገራቸውን የም/ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
ጣልያን እና ኢትዮጵያ በስደተኞች ፍልሰት አስተዳደር፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በትብብር እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለሰላም ያላት ቁርጠኝነት ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው÷በቀጣናው ሰላም እንዲሰፍን ኢትዮጵያ የበኩሏን ጉልህ ሚና መወጣት እንደሚጠበቅባትም ተናግረዋል፡፡