Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የማንችስተር ዩናይትድ የቀድሞ ኮከብ ተጫዋች ሉዊስ ናኒ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጣ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድንና የማንችስተር ዩናይትድ ተጫዋች የነበረው ሉዊስ ናኒ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ የመቻል ስፖርት ክለብ አስታወቋል፡፡

ሉዊስ ናኒ የመቻል ስፖርት ክለብ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ በክብር እንግድነት ለመታደም ነው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው፡፡

የመቻል ስፖርት ክለብ ቦርድ ሰብሳቢ ሰይፉ ጌታሁን (ዶ/ር)÷የመቻል ስፖርት ክለብን 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች ማክበር የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

የ37 ዓመቱ የፖርቹጋል ብሄራዊ ቡድንና የማንችስተር ዩናይትድ ተጫዋች የነበረው ሉዊስ ናኒ ሐምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም በክለቡ የምስረታ በዓል ለመገኘት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ጠቁመዋል።

ናኒ ያቋቋመው የስፖርት አካዳሚ ከመቻል ጋር የትብብር ሥምምነት እንደሚፈራረምም ነው የገለጹት፡፡

የ37 ዓመቱ ፖርቹጋላዊ የክንፍ መስመር ተጫዋች ናኒ ማንችስተር ዩናይትድ፣ ቫሌንሺያ፣ ላዚዮ፣ ስፖርቲንግ ሊዝበንና ፊነርባቼ ከተጫወተባቸው ክለቦች መካከል ይጠቀሳሉ።

በሌላ በኩል ክለቡ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የመርሐ ግብር አካል የሆነ የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ እንደሚካሄድና በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል።

ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ደግሞ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ባለኃብቶች የሚሳተፉበት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር እንደሚካሄድ ጠቅሰዋል፡፡

ሐምሌ 7 ቀን 2016 ዓ.ም መቻል ከዩጋንዳው ኪታራ ስፖርት ክለብ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያካሄድ መጠቆማቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡

የመቻል ስፖርት ክለብ በ1936 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን÷ እግር ኳስና አትሌቲክስን ጨምሮ በልዩ ልዩ የስፖርት አይነቶች ሥመ-ጥር ስፖርተኞችን ያፈራ የስፖርት ክለብ መሆኑ ይታወቃል።

Exit mobile version