የሀገር ውስጥ ዜና

ኢንስቲትዩቱ ጥራት ያለው አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ሲሰራ መቆየቱን ገለጸ

By Shambel Mihret

June 27, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለፉት ዓመታት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር፣ የላቦራቶሪ አቅም በመገንባት ጥራት ያለው የላቦራቶሪ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ሲሰራ መቆየቱን ገለጸ፡፡

ኢንስቲትዩቱ “የምዕተ-ዓመት ጥረት ለተሻለ ሕብረተሰብ ጤና” በሚል መሪ ሃሳብ የ100ኛ ዓመት አልማዝ ኢዮቤልዩ ክብረ-በዓል የማስጀመሪያ መርሐ ግብርን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በወቅቱ እንዳሉት÷ ኢንስቲትዩቱ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቅኝት፣ መከላከልና ምላሽ ሥራዎችን እየሰራ ነው፡፡

በበሽታ አምጪ ተህዋስያን የሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎች ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የቁጥጥር ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ ቀደም የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተሰራው ሥራ ተጨባጭ ውጤት ማስገኘቱን ተናግረዋል።

በተለይም ወባን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተሰራ ስራ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን አስረድተው፤ በአስተላላፊ ትንኞች የሚተላለፉ በሽታዎች ሲከሰቱ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የወባ በሽታ ላይ ሀገራዊ ንቅናቄ በመፍጠር እስከታችኛው መዋቅር ድረስ አደረጃጀት በማጠናከር በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ 222 ወረዳዎች ተለይተው በየቀኑ መረጃ በመለዋወጥ የወባ በሽታን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራው እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ኢንስቲትዩቱ ባለፉት 100 ዓመታት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር፣ የሀገራዊ የላቦራቶሪ አቅም በመገንባት ጥራት ያለው የላቦራቶሪ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ሲሰራ መቆየቱንም ተናግረዋል።

የ100 ዓመታት ክብረ-በዓሉም ኢንስቲትዩቱ የጀመራቸውን ውጤታማ ሥራዎች የሚያጠናክርበትና ያለውን አህጉርና ዓለም ዓቀፍ ትስስር አጠናክሮ የሚቀጥልበት ነው መባሉን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡