የሀገር ውስጥ ዜና

በዩኒቨርሲቲው “ስማርት ካምፓስ ሶሉሽን”ን ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ተደረገ

By Amele Demsew

June 27, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስማርት ካምፓስ ሶሉሽን ለማቅረብ እንዲሁም የጥቁር አንበሳ አጠቃላይ ስፔሻላይድ ሆስፒታል የህክምና አገልግሎት ክፍያዎችን በቴሌብር እንዲፈጽም የሚያስችል ስምምነት ተደረገ፡፡

ቴክኖሎጂው የዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማርና የአስተዳደር ስራዎች ዲጂታላይዝድ የሚያደርግ መሆኑ ተጠቁሟል።

የስማርት ካምፓስ ሶሉሽን የዩኒቨርሲቲውን የመማሪያ ክፍሎች ዲጂታል ማድረግ የተለያዩ ካምፓሶችን ደህንነት መቆጣጠሪያ ሲሲቲቪ ካሜራ፣የኔትወርክ መሰረተ ልማቶችን መዘርጋት እና ሌሎች ዘመናዊ አሰራሮችን መተግበር የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ÷ ፕሮጀክቱ ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ሲገባ ዩኒቨርሲቲውን ብቁና ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) በበኩላቸው÷ፕሮጀክቱ ዩኒቨርሲቲው የጀመረውን የሪፎርም ስራ ከማገዝ በተጨማሪ የአካዳሚክ ልህቀትን ለማምጣት፣የትምህርት ጥራትን ለማሳደግና ምርምርን ለማጎልበት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በቅድስት አባተ