የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል የዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው

By Amele Demsew

June 27, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የ2ኛው ምዕራፍ የ2ኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደን ጨምር የክልሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ከዞን እስከ ወረዳ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

በመርሃ ግብሩ በአማራ ክልል ባለፉት 5 ዓመታት 7 ቢሊየን ችግኞች መትከል መቻሉ ተገልጿል።

ባለፉት ዓመታት በተተገበረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአፈር መከላት መቀነሱ፣ የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር ውሃ መጨመሩን እንዲሁም የደን ሽፋን ከ 14 ነጥብ 3 በመቶ ወደ 15 ነጥብ 74 በመቶ ማደጉ ተገልጿል።

እንዲሁም በአረንጓዴ አሻራ ሥራ ከለሙ ተፋሰሶች በፍራፍሬ፣ በደን ልማት፣ በንብ ማነብና በከብት ማድለብ ከ 752 ሺህ በላይ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸው በመድረኩ ተነስቷል።

የዘንድሮውን ክልላዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ያስጀመሩት ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ÷የአረንጓዴ አሻራ ስኬት አስተማማኝ እንዲሆን የተተከሉትን ችግኞች መንከባከብና የዓመቱን 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ችግኞችን የመትከል እቅድ ለማሳካት ርብርብ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

መርሃ ግብሩ ከዛሬ ጀምሮ በመላው የክልሉ ዞኖች፣ ወረዳዎችና፣ ቀበሌ ማዕከላት በይፋ የተጀመረ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

በደሳለኝ ቢራራ