አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና 5 ወርቅ፣ 4 ብር እና 1 የነሐስ ሜዳልያ በማግኘት ውድድሩን አጠናቅቃለች፡፡
በካሜሩን አስተናጋጅነት በዱዋላ ከተማ ከ27 ሀገራት በላይ የተውጣጡ 2 ሺህ 500 አትሌቶች ላለፉት 6 ቀናት ሲሳተፉበት የነበረው 23ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር ተጠናቅቋል።
ኢትዮጵያም በ32 ሴት እና በ36 ወንድ አትሌቶች በ19 የአትሌቲክስ የውድድር አይነቶች በመሳተፍ 5 ወርቅ፣ 4 ብር እና አንድ ነሐስ በድምሩ 10 ሜዳልያዎች በማግኘት አጠናቅቃለች።
አትሌት ፋንታዬ በላይነህ በ5 ሺህ ሜትር ሴቶች፣ ንብረት መላክ በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች፣ ምስጋና ዋቁማ በወንዶች በ20 ኪሎ ሜትር እርምጃ፣ ስንታየሁ ማስሬ በሴቶች በ20 ኪሎ ሜትር እርምጃ እና ሳሮን በርሄ በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝተዋል፡፡
እንዲሁም ውብርስት አስቻል በ5 ሺህ ሜትር ሴቶች፣ ገመቹ ዲዳ በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች፣ አለምናት ዋለ በ3 ሺህ ሜትር መሠናክል ሴቶች እና አትሌት ንብረት መላክ በ5 ሺህ ሜትር ወንዶች የብር ሜዳልያ አስገኝተዋል፡፡
በተጨማሪም አትሌት ገላ ሃምበሴ በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች የነሐስ ሜዳልያ ማስገኘቷን የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡