አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት 11 ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ ቅመማቅመም ምርት 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ከ50 በላይ ቅመማቅመሞች እንደሚመረቱ ጠቁመው÷ ከእነዚህ ውስጥም 16ቱ ለዓለም ገበያ ይቀርባሉ ብለዋል፡፡
ለዚህም ኮረሪማ፣ ዕርድ፣ ጥምዝ፣ ቁንዶ በርበሬ እና በርበሬ ያሉ ቅመሞች ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ምርቶችም ወደ 39 የተለያዩ ሀገራት እንደሚላኩ ነው ዋና ዳይሬክተሩ የጠቀሱት፡፡
በበጀት ዓመቱ 11 ወራት 8 ሺህ 400 ቶን ቅመማቅመም ወደተለያዩ የዓለም ሀገራት በመላክ 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር መገኘቱን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡
አፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር በመጠን ሲነጻጸር ከ2 ሺህ ቶን በላይ ብልጫ ማሳየቱንም ተናግረዋል፡፡