Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ ዳኞችና ተሿሚዎች ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ክልል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የስነ ምግባር ጉድለት ክስ በተመሰረተባቸው የፍርድ ቤቱ ዳኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች ላይ የስራ ስንብት እና የደሞዝ ቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል።

ጉባኤው ባለፉት ወራት ከማህበረሰብ የቀረቡ ቅሬታዎችንና የምርመራ ውጤቶችን መነሻ በማድረግ የፍርድ ቤቱ ዳኞች ስነ-ምግባር ደንብን በመተላለፍ የዲሲፕሊን ጥፋት በፈፀሙ ዳኞችና የጉባኤ ተሿሚዎች ላይ ክስ ተመስርቶ ለክልሉ ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የቀረበ መሆኑን አስታውሷል።

ጉባኤው የቀረበለትን የስነ ምግባር ጉድለት ክስና ማስረጃዎች ከህጉ አንፃር አገናዝቦ በመመርመር ከቀረቡለት 13 ክሶች መካከል 10 ክሶች ላይ ጥፋት መፈፀሙን በማረጋገጥ ክስ የቀረበባቸው 5 ዳኞች እና 4 የጉባኤ ተሿሚዎች ጥፋተኛ ናቸው ሲል ውሳኔ ሰጥቷል።

እንዲሁም 3 ክሶች በቂ ማስረጃ ያልቀረበባቸው በመሆኑ ውድቅ ያደረጋቸው መሆኑን አስታውቋል።

በዚህም ጥፋተኛ የተባሉ 1 የሸሪአ ፍርድ ቤት ዳኛና 2 ተሿሚዎች ከስራ እንዲሰናበቱ የተወሰነ ሲሆን÷1 የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ፣ 2 የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞችና 1 ዳኛ በአራት ወር ደሞዝ እንዲቀጡ፣ 1 የተከላካይ ጠበቆች አስተባባሪ ከደሞዝና ደረጃ ዝቅ እንዲል እና 1 ባለሙያ የሶስት ወር ደሞዝ እንዲቀጡ ጉባኤው የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል።

የክልሉ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች ማኔጅመንት ባከናወነው ግምገማ ክፍተት አለባቸው ተብለው በተለዩ መደቦች ላይ ለዳኞች እና ለጉባኤ ተሿሚዎች የስራ ድልድል አከናውኗል።

በዚሁ መሠረት በቀረበባቸው የዲሲፕሊን ክስ ጥፋተኛ ተብለው የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸዉ 3 ዳኞች ከዳኝነት ስራ ተነስተው በሌሎች የአስተዳደር ስራዎች ላይ እንዲመደቡ መደረጉም ተጠቁሟል፡፡

በቀጣይ የተጠያቂነት ስርዓትን በማጠናከር ከመሠረታዊ የብቃት ማነስና ከስነ-ምግባር ብልሹነት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ህግና ስርዓትን ተከትሎ እንዲቀረፉ በማድረግ የማጥራቱን ስራ ለመተግበር ጉባኤው በቁርጠኝነት እንደሚሰራ መገለጹን የክልሉ ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ መረጃ ያመላክታል።

Exit mobile version