Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በባሕር ዳር ሲካሄድ የቆየው የሰላም ኮንፈረንስ ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ባሕር ዳር ከተማ ላለፉት ሁለት ቀናት ‘ሰላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሰላም’ በሚል መሪ ሀሳብ ሲካሄድ የቆየው የሰላም ኮንፈረንስ ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣትተጠናቅቋል።

በኮንፈረንሱ ከሁሉም የክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች የተውጣጡ የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ ወጣቶችና ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተሳትፈዋል፡፡

ኮንፈረንሱ በክልሉ የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም በማምጣት የክልሉን ሕዝብ የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያለመ እንደነበር ተገልጿል፡፡

በዛሬው ዕለትም ኮንፈረንሱ ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት  መጠናቀቁ ተመላክቷል፡፡

የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች በአቋም መግለጫቸው እንደገለጹት÷ታጥቀው የሚታገሉ ሃይሎች ለሕዝብ ሰላምና ደህንነት ሲባል ከሕዝባቸው ጋር ተስማምተው ወደ ሰላማዊ ውይይትና ድርድር እንዲመጡ  ጠይቀዋል።

ሕዝቡ በሰላም እጦቱ ምክንያት እየደረሰበት ያለውን እንግልት በማቆም በሙሉ አቅሙ ወደ ልማት እንዲመጣም የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ  ተናግረዋል።

ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና በክልሉ ያለውን ሁኔታ ከመሰረቱ ለመቀየር ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል በቀናነት ትብብር እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

የአቋም መግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

1. በሰላምና በፀጥታ፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በማንነትናበራስ አስተዳደር ጉዳይ እንዲሁም ህገመንግስትን ስለማሻሻል አስመልክቶ ያነሳናቸውን ጥያቄዎች በየፈርጃቸው ለፌደራል መንግስትና ለክልሉ መንግስት እንዲቀርብልን ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ ሁሉም ጥያቄዎች በአንድ ጊዜ እንደማይመለሱ ስለምናምን መንግስት የህዝቡን ጥያቄ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት እንዲሁም በፍጥነት መመለስ ያለባቸውን ለመፍታት የሚኖረውን ዝግጁነት በጋራ እያየን እንዲሁም በሰላማዊ መንገድ እየተወያየን ጥያቄዎቹ እንዲፈቱልን መጠየቃችንን እንቀጥላለን፡፡

2. በክልሉ ውስጥ በርካታ የልማት ጥያቄዎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ የልማት ጥያቄዎች ያለ ሰላም ሊታሰቡ ስለማይችሉ ቅድሚያ በክልላችን ውስጥ ማንኛውም ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት በውይይታችን የተስማማን መሆኑን እናሳውቃለን፡፡
3. ለሚድያ ተቋማትና ሙያተኞች እንዲሁም ለማህበረሰብ አንቂዎች የክልሉ ህዝብ በርካታ ሁለንተናዊ ችግሮች ተጋርጠውበት ቆይተዋል፡፡ በርካታ ምስቅልቅሎችም ደርሰውበታል፡፡ ስለሆነም ይህን ዘርፈ ብዙ ችግር ተገንዝባችሁ ህዝቡን ወደ ሰላም የሚመልስና የክልሉ ህዝብ ከሌሎች ወንድምና እህት ህዝቦች ጋር በጋራ የገነባናት ሃገር ተከባብሮና በነፃነት ተዘዋውሮ እንዲሰራባት ለማስቻል የሚድያውን አየር በሰላም እንዲትሞሉልን በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን፡፡
4. የመንግስት ባለስልጣናት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራን፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎች፣ እንዲሁም መላ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ፤ በልልላችን ከተፈጠረው ቀውስ በመውጣት አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በምናደርገው ጥረት ለክልላችን ሰላም ስትሉ ሁሉንም አይነት የሰላም ድጋፍ እንዲታደርጉ፣ ከመገፋፋትና ከመጠላለፍ በመውጣት ለክልሉ ህዝብ ሰላማዊ እንቅስቃሴ በጋራ እንዲትቆሙ እንጠይቃችኃለን፡፡
5. ታጥቃችሁ ጫካ የገባችሁ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እንታገልለታለን የምትሉት ህዝብ ያለበትን ችግርና የክልሉ ህዝብ ህልውና እንዴት እንደተፈተነ በግልፅ ታውቃላችሁ፡፡ ስለሆነም ጥያቄያችሁን በሰላማዊ መንገድ በውይይትና በድርድር እንዲታቀርቡ እንዲሁም የወገናችሁን ስቃይ ለመቀነስ እንዲቻል መገዳደል ይብቃን ብላችሁ ወደ ወገኖቻችሁ እንዲትቀላቀሉ የሰላም ኮንፈረንሳችን ተሳታፊ በሙሉ ወገናዊ ጥሪ እያስተላለፍን መንግስትም ሆደ ሰፊ በመሆን እነዚህ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር በመወያየት እና በመደራደር ለህዝባችን ሰላም ሲባል በይቅርታና በክብር እንድቀበላቸው ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
6. የክልል መንግስታት፣ እንዲሁም የዞንና የከተማ አስተዳደሮች በምታገለግሉት ህዝብ ውስጥ የክልላችን ተወላጆች እናንተን የመንግስት አስተዳደሮችን እና አብሮ ለዘመናት የኖረውን ወገኖቹን አምኖ እየኖረ መሆኑን በመገንዘብ ህዝባችን ባይተዋርነትና ብቸኝነት እንዳይሰማው፣ ጥቃት እንዳይደርስበት፤ በክልላችን ለሚኖረው ህዝብ የጥያቄ ምንጭ እንዳይሆን እንድሁም የሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደታችንን በአስተማማኝ ሁኔታ መሰረት እንድኖረዉ በጋራ እንድንቀሳቀስ በሰላም ኮንፈረንሳችን ጥሪያችንን እያሰተላለፍን በአማራ ክልል ማንኛውም ዜጋ በብሄሩ ወይም በእምነቱ ወይም በሌሎች ምክንያቶች የማይገለልበት ክልል እንድሆን እኛም እንደቀደመው ሁሉ እንደምንሰራ ቃል እንገባለን፡፡
7. በክልላችን ውስጥ የምትንቀሳቀሱ የፌደራልና የክልል የፀጥታ ሀይሎች በማንም ይጠንሰስ ማንም ይጀምረው በክልላችን ውስጥ እየሆነ ያለው ነገር ወንድም ወንድሙን እየገደለና ህዝባችን የከፋ ችግር እየደረሰበት መሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም የጀመርነው የሰላም ጥረት እንዲሳካ የበኩላችሁን ጥረት እንድታደርጉና ከጫካ የሚመጡ ወንድሞቻችሁ ወንድም መሆናቸውን አውቃችሁ በፍፁም ሙያዊ ዲስፕሊንና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት አቀባበል ታደርጉላቸው ዘንድ የከበረ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
8. በጫካ የሚገኙ ወንድሞቻችን በሰላማዊ መንገድ በውይይትና በድርድር ወደ ማህበረሰቡ ከተቀላቀሉ በኃላ የሃገራችንን ሁለንተናዊ ችግር በዘላቂነት ይፈታል ተብሎ በታሰበውና ተስፋ በተጣለበት የሃገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ በማድረግ ያላቸውን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ አቅርበው የህዝቡን ችግር በትክክለኛው መንገድ እንዲፈታ በማድረግ ታሪካዊ ሃላፊነታቸውን እንድወጡ ሁሉም አካል የበኩሉን እንድወጣ ጥሪያችንን እናሰተላልፋለን፡፡
9. በክልሉ ውስጥ ከተፈጠረው ችግር ጋር ተያይዞ ተጠርጥረው በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ዜጎች ማለትም ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ምሁራን፣እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪ ዜጎች በክልሉ ውስጥ ለምንገነባው ዘላቂ ሰላም የበኩላቸውን እንድወጡ ለማስቻል መንግስት በይቅርታና በምህረት ነፃ እንዲወጡ በማድረግ ሚናቸውንና ድርሻቸውን እንዲወጡ እንጠይቃለን፡፡
10. በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል የተደረገውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት መንግስት በሆደ ሰፊነት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ማድረጉ ይታወሳል፡፡ የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ የፊደራል መንግስትና የክልላችን መንግስት ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ በሚገኙበት በዚህ ወቅት በህወሀት በኩል ገና ከጅምሩ ጀምሮ ስምምነቱን እንደ ጊዜ መግዣ በመጠቀም የማንነት እና የራስ አስተዳደር ጥያቄ ባለባቸዉ አካባቢዎች ወረራ በመፈፀም ላይ ይገኛል ፡፡ በመሆኑም መንግስት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊና ተፈፃሚ እንዲሆን በማድረግ ወራሪ ሀይሎች ከወረሩበት ቦታ በፍጥነት እንዲወጡ እንድሁም ጥያቄዎች በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ እልባት እንዲሰጣቸው ስንል የሰላም ኮንፈረንሳችን ይጠይቃል፡፡

በደሳለኝ ቢራራ

Exit mobile version