ስፓርት

ፈረንሳይ፣ እንግሊዝና ኔዘርላንድስ ጥሎ ማለፉን ለመቀላቀል ብርቱ ፍልሚያ ይጠብቃቸዋል

By ዮሐንስ ደርበው

June 25, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ የዛሬ መርሐ-ግብሮች ጥሎ ማለፉን ለመቀላቀል የሚያስችሉ ጠንካራ ፉክክር የሚጠብቃቸው አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡

በዚህ መሠረትም ምሽት 1 ሠዓት ላይ በቡድን አራት የተደለደሉት ፈረንሳይ ከፖላንድ እንዲሁም ኔዘርላንድስ (ሆላንድ) ከኦስትሪያ በተመሳሳይ ሠዓት ይጫወታሉ፡፡

ምድብ አራትን የምትመራው ኔዘርላንድስ ኦስትሪያን የማሸነፍ ዕድል እንዳላትም ቅድመ-ጨዋታ ግምቶች እየተሠነዘሩ ነው፡፡

አራት ነጥብ በመያዝ በዚሁ ምድብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ፈረንሳይ ፖላንድን እንደምታሸንፍም በርከት ያሉ ግምቶች እየተሰጡ ነው፡፡

ኦስትሪያ ሦስት ነጥብ ሲኖራት፤ ያለምንም ነጥብ በምድቡ ግርጌ ላይ የምትገኘው ፖላንድ ከአውሮፓ ዋንጫ የተሰናበተች ሀገር ሆናለች፡፡

በሌላ በኩል ምሽት 4 ሠዓት ላይ በምድብ ሦስት የሚገኙት ዴንማርክ ከሠርቢያ እና እንግሊዝ ከስሎቬኒያ ይፋለማሉ፡፡

ምድቡን እንግሊዝ በአራት ነጥብ ስትመራ÷ ዴንማርክ እና ስሎቬኒያ በተመሳሳይ ሁለት ነጥብ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡

ሠርቢያ ደግሞ አንድ ነጥብ በመያዝ በዚሁ ምድብ መጨረሻ ላይ ትገኛለች፡፡

የምድብ ሦስትን ጨዋታዎች ዴንማርክ እና እንግሊዝ የማሸፍ ዕድል እንዳላቸው ቅድመ-ጨዋታ ግምቶች እየተበራከቱ ነው፡፡

እስከ አሁን የ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ አስተናጋጅ ጀርመን፣ ስዊዘርላንድ፣ ጣልያን፣ ስፔን እና ፖርቹጋል ጥሎ ማለፉን (ምርጥ 16) መቀላቀላቸውን ያረጋገጡ ብሔራዊ ቡድኖች ናቸው፡፡