አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ተክለ ትኩዕ አስመጪና ላኪ ከህንዱ ፒያጆ ኩባንያ ጋር በመተባበር የከፈተው የባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ ፋብሪካ ይፋዊ ስራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
በመርሃ ግብሩ የተክለ ትኩዕ አስመጪና ላኪ ባለቤት ተክለ ትኩዕ ÷ ድርጅቱ ከህንድ አስመጥቶ በመገጣጠም ለገበያ እያቀረበ የሚገኘው የህዝብና የጭነት ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎችን ነው ብሏል።
የፒያጆ ኩባንያ ስራ አስኪያጅ ዲያጎ ግራፊ በበኩላችው÷ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ ምርቱን መሸጥ መጀመሩ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።
የጭነት ተሽከርካሪዎቹ ከ230 ሲሲ እስከ 435 ሲሲ እንዳላቸው የተገለጸ ሲሆን÷ እስከ 10 ኩንታል የመሸከም አቅም እንዳላቸው ተጠቁሟል፡፡
የህዝብ ተሽከርካሪዎቹም በተመሳሳይ ከ230 እስከ 435 ሲሲ የሆኑ ከ3 ሰው እስከ 10 ሰው የመጫን አቅም ያላቸው መሆናቸው ተነስቷል፡፡
ተሽከርካሪዎቹ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በወኪሎች እየተሸጡ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ÷በሊትር እስከ 45 ኪሎሜትር የመጓዝ አቅም እንዳላቸው ተጠቅሷል።
በቤንዚንና በናፍጣ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ የተሽከርካሪ አይነቶችን አስመጥቶ መገጣጠም የጀመረው ድርጅቱ ሙሉ መገጣጠሚያና የጥገና አገልግሎት እንደሚሰጥም ተገልጿል።
ድርጅቱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አስመጥቶ ለመገጣጠም እቅድ እንዳለውም ተገልጿል፡፡
በሃይማኖት ኢያሱ