የሀገር ውስጥ ዜና

ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) መድኃኒቶችን በራስ ዐቅም ማምረት ለነገ የሚተው አለመሆኑን አስገነዘቡ

By Tamrat Bishaw

June 22, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ120 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ላላት ኢትዮጵያ መድኃኒቶችን በራስ ዐቅም ማምረት ለነገ የሚተው ጉዳይ አይደለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገር ውስጥ የሕክምና ግብዓት ምርትና ኢኖቬሽን ዐውደ-ርዕይን መርቀው ከፍተዋል፡፡

ይህን ተከትሎም በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ የሀገር ውስጥ የሕክምና ግብዓቶችንና እና መድኃኒቶችን ለማምረት የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ከማድረግ ጀምሮ ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

እንዲሁም መድኃኒት እና የሕክምና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን አስቻይ ሁኔታዎች መዘጋጀታቸውን በዐውደ-ርዕዩ ላይ ባደረጉት ንግግር አስታውቀዋል፡፡

”ጤናችን በምርታችን” በሚል መሪ ሐሳብ የተከፈተውን ዐውደ-ርዕይ የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ መድኃኒት አምራቾች ማኅበር በጋራ አዘጋጅተውታል፡፡

ለሥድስት ቀናት ለሕዝብ ክፍት ሆኖ በሚቆየው ዐውደ-ርዕይ ላይ÷ ከ110 በላይ የዘርፉ አምራቾች እንደሚሳተፉበት ተገልጿል፡፡