የሀገር ውስጥ ዜና

ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ሣምንት ተከፈተ

By Tamrat Bishaw

June 22, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) “ቴክኒክና ሙያ ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀው 14ኛው ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ሣምንት ተከፈተ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ክኅሎት መር አቅጣጫ ተከትለው እንዲሠሩ ድጋፍና ክትትል እያደረግን ነው ብለዋል፡፡

በዚህም ፍትሐዊ የሥራ ዕድል ከመፍጠር በተጨማሪ ምርታማነትን ማሣደግ ችለናል ነው ያሉት፡፡

የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ኢንተርፕራይዞቻችን እንዳይከስሙ፣ አባሎቻቸው በጠንካራ የሥራ ባህልና ክኅሎት እየታነጹ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ተኪ ምርት አምርተው ለገበያ በማቅረብ፣ የዋጋ ንረቱን በመግራትና የውጭ ምንዛሬ በማዳን አስተዋጽዖ አበርክተዋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ተቋማቱ ከማሰልጠን ባሻገር ተስማሚና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን እየለዩ በማላመድና በማሰልጠን ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው÷ በተቋሞቻቸው የተገኙ ውጤቶችን በዐውደ-ርዕዩ ያቀርባሉ ብለዋል፡፡

የመዲናዋ ነዋሪዎችም ከዛሬ ጀምሮ ለሥድስት ቀናት የሚቆየውን ዐውደ-ርዕይ እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡