አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሩሲያ አዘጋጅነት ሲካሄድ የቆየው የብሪክስ አባል ሀገራት ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶች የተሳተፉበት ፎረም ተጠናቀቀ፡፡
ፎረሙ ከሰኔ 10 እስከ 14 ቀን 2016 ዓ.ም “ብሪክስ ቺፍ ጀስቲስ ፎረም” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ነው የተካሄደው፡፡
በመድረኩም÷ በፍርድ ቤቶች አሠራር፣ በዜጎች የማኅበራዊ መብቶች አጠባበቅ፣ በኢንቨስተሮች መብት ጥበቃ፣ በመሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች ጥበቃ ላይ ምክክር ተደርጓል፡፡
እንዲሁም በወንጀል ፍትሕ ሥርዓት፣ የፍርድ ቤቶችን አሠራር የሚያዘምን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና የብሪክስ አባል ሀገራት ሕግጋት ላይ የጋራ ግንዛቤ መፍጠር ዙሪያ ውይይት መደረጉን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምኅረት በአቅም ግንባታ ረገድ÷ ከሩሲያ በተጨማሪ ከሕንድ፣ ቻይና እና ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች አቻዎቻቸው ጋር በትብብር በሚሠሩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡