Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በመዲናዋ በ120 ወረዳዎች የአከራይ ተከራይ ውል ምዝገባ እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ120 ወረዳዎች የአከራይ ተከራይ ውል ምዝገባ እየተከናወነ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ ገልፀዋል።

ኃላፊዋ ሰኔ 1 ቀን 2016 የተጀመረው የአከራይ ተከራይ የውል ስምምነት በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

አዋጁ አከራዩን እና ተከራዩን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ያሉት ኃላፊዋ ÷ የተከራዮችንም የመክፈል አቅም ያገናዘበ ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ ኖሮት እንዲመዘገብ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ተሰርቷልም ነው ያሉት።

የቢሮው ኃላፊ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ በቀሪ 15 ቀናት ዜጎች በአቅራቢያቸው በሚገኙ ወረዳዎች በማቅናት ምዝገባ እንዲያካሂዱ አሳስበዋል።

አከራዮች የውል ስምምነቱን ሳይፈጽሙ እስከ 3 ወር ድረስ ከቆዩ የ2 ወር የቤት ኪራይ እንዲከፍሉ እንደሚደረግም ኃላፊዋ ተናግረዋል።

አሁን ላይ ይህንን ስራ ብቻ የሚያከናውን ቡድን መቋቋሙን ገልጸው አገልግሎቱ ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ በምሽት ጭምር እየተሰጠ ነው ብለዋል።

ይህንን ተከትሎም የተሰጠው የምዝገባ ጊዜ በቂ በመሆኑ የቀን ጭማሪ ላይኖር ይችላል ብለዋል።

ከመጋቢት 24 ጀምሮ የሚደረግ የቤት ኪራይ ጭማሪ እና ውል ማቋረጥ ክልክል ነው ተቀባይነት የለውም ሲሉም አክለዋል።

መንግስት ጥናት በማድረግ በሚቀጥለው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የዋጋ ጭማሪ ያደርጋልም ነው ያሉት።

አከራይ የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ ማድረግ የሚችለው በዓመት አንዴ መንግስት በሚያወጣው ተመን እንደሚሆንም አንስተዋል።

በመሳፍንት እያዩ

Exit mobile version