የሀገር ውስጥ ዜና

ዘንድሮ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን በጋራ መትከል ይኖርብናል – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

By Tamrat Bishaw

June 21, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዘንድሮ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን በጋራ መትከል ይኖርብናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።

የ2016 ዓ.ም ዙር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ቅድመ ጅማሮ መርሃ ግብር ዛሬ ተካሂዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ በአረንጓዴ ዓሻራ ጥረቶቻችን አማካኝነት ልናሳካው ለምንፈልገው ለውጥ የአመለካከት እና የአዕምሮ ውቅር ሽግግር ያስፈልገናል ብለዋል።

እንደ ሀገር ልናሳካ ካለምነው 50 ቢሊዮን ችግኞች በያዝነው አመት 40 ቢሊዮን ችግኞች ላይ ለመድረስ እየጣርን በመሆኑ በዘንድሮው የተከላ ዙር 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን በጋራ መትከል ይኖርብናል ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ለነገው ትውልድ ቅርስ ለመተው የሚሻ ሁሉ ዛሬ ላይ ማዋጣት የግድ ይለዋል ሲሉም አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ላለፉት አምስት አመታት በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተጠነሰሰው የአረንጓዴ ዓሻራ መርሃ ግብር አማካኝነት በየአመቱ የችግኝ ተከላ ስራ ስታካሂድ መቆየቷን ያስታወሰው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ፤ የባለፉት አመታት ጥረትን በማጤን የ2016ቱን ዙር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ቅድመ ጅማሮ መርሃ ግብር መካሄዱን ገልጿል።

በመርሃ ግብሩ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ሪፖርት ይፋ መሆኑን እና የሀገራዊውን የአረንጓዴ አሻራ ይዘት እና የስራ ውጤት በሰዋዊ ተረክ የሚያቀርብ ዓለም አቀፍ ዘጋቢ ፊልም የምረቃ እይታ ተካሂዷል።

ይፋ የተደረገው የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ሪፖርት እንዳመለከተው የደን ሽፋናችን በ2011 ዓ.ም ከነበረበት 17 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማለቱ ይፋ ሆኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመርሃ ግብሩ ባደረጉት ንግግር ይህንን የዕድገት ውጤት ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።