የሀገር ውስጥ ዜና

ከ7 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች የት/ቤት ምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆኑ

By Feven Bishaw

June 21, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት10 ወራት 7 ነጥብ 88 ሚሊየን ተማሪዎችን የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል፡፡

አገልግሎቱ በ10 ወራት በትምህርት ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችን አስመልክቶ ባወጣው መረጃ÷ በት/ቤት ምገባ መርሐ ግብር 9 ሚሊየን ተማሪዎችን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ 7 ነጥብ 88 ሚሊየን ተማሪዎችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን አንስቷል፡፡

በሌላ በኩል 22 ነጥብ 7 ሚሊየን የሁለተኛ ደረጃ መጽሐፍት መታተማቸው ነው የተገለጸው፡፡

ትምህርት ለትውልድ በተሰኘው ሀገር አቀፍ የት/ቤቶች ማሻሻያ ንቅናቄ መርሐ-ግብርም የ5 ሺህ 873 አዳዲስ ት/ቤቶች ግንባታና የ14 ሺህ 791 ት/ቤቶች ጥገና ሥራ መከናወኑ ተጠቅሷል፡፡

የመውጫ ፈተና አተገባበር ሒደትን በተመለከተም ፈተናውን ከወሰዱ 97 ሺህ 673 ተማሪዎች ውስጥ 27 ሺህ 35 ወይም 27 ነጥብ 67 በመቶ የሚሆኑት ማለፋቸው ተመላክቷል ።

በ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተናን በወረቀትና በኦንላይን መስጠት የሚቻልበት አቅም መፈጠሩን አገልግሎቱ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡

በትምህርት ማስረጃ ማረጋገጥ ሥራም ከ136 የፌዴራል ተቋማት ለ18 ሺህ 326 ሰራተኞች የትምህርት ማስረጃ ትክክለኛነት ተረጋግጧል ነው የተባለው፡፡

በትርክት ግንባታ ረገድም የግብረ-ገብ ትምህርት በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ተካትቶ መሰጠት መጀመሩም ተጠቁሟል፡፡

ለጎረቤት ሀገራት የሚሰጡ የነጻ ትምህርት እድሎችን ከማሳደግ አንጻርም ኢትዮጵያ በ2016 ዓ.ም 865 ተማሪዎችን ተቀብላ በማስተማር ላይ ትገኛለች ተብሏል፡፡