የሀገር ውስጥ ዜና

ከችግር ለመውጣት ተስማምተንና አንድ ሆነን መሥራት መቻል አለብን – አቶ አረጋ ከበደ

By Melaku Gedif

June 21, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከችግር ለመውጣት ተስማምተንና አንድ ሆነን መሥራት መቻል አለብን ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች የውይይት መድረክ እየተካሄደ ሲሆን በመድረኩ የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ም/ቤት አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

በውይይቱ መልዕክት ያስተላለፉት አቶ አረጋ ከበደ÷ ጊዜው የመሪዎችን ቁርጠኝነት እንደሚፈልግ ገልጸዋል።

ፈተና የበዛባቸው ወቅቶች ቁርጠኝነትን እንደሚፈጥሩ አንስተው÷ የመሪዎች ቁርጠኝነት የሚገለጸው በተግባር መሆኑንም አመላክተዋል።

መሪዎች በሁሉም ዘርፍ ድጋፍ እንዲያደርጉ እና ችግሮችን እንዲለዩ ወደ ዞኖች ተሠማርተው እንደነበር ጠቅሰው÷ መሪዎቹ ችግር በመለየት ችግር እንዲፈቱ ሚና ተሰጥቶቿው እንደነበር ገልጸዋል።

የገጠመውን ችግር በመፍታት እና በማስተካከል ቀደም ሲል የነበሩ መደበኛ ሥራዎች እንዴት እየሄዱ እንደሆነ እንደሚገመገሙም ገልጸዋል።

በአስተሳሰብ እና በአተገባበር ሒደት የተደራጀ አካሄድ ስለመኖሩም እንደሚገመገም መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

በየደረጃው ያለው መዋቅር የተግባር አንድነትን ማጠናከር፣ በተገቢው መንገድ መምራት ይገባል ብለዋል።

ከፍተኛ አመራሮች የሚሠሯቸው ሥራዎች በመካከለኛ እና በዝቅተኛ መሪዎች ተጽዕኖ እንዳለው ጠቁመው÷ የላይኛው መዋቅር በተገቢው መንገድ መሥራት እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።

እያለቀ ባለው በጀት ዓመት በተፈጠረው ችግር ምክንያት በርካታ ሥራዎች መደነቃቀፋቸውን የገለጹት ርዕሰ መሥተዳደሩ÷ መሥራት የሚገባንን ባለ መሥራታችን የተፈጠሩ ችግሮችን በክረምቱ ወቅት መቀነስ ይገባናል ብለዋል።

በችግሮች ላይ መነጋገር፣ አቅጣጫ ማስቀመጥ እና ለመፍታት መረባረብ ይገባናል በማለት ገልጸው፤ በክልሉ የሚነሱ ችግሮች እንዲፈቱ ኀላፊነቱ የተጣለው በክልሉ መሪዎች ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ እና ከክልሉ ውጭ ያሉ ችግሮችን አይመለከተኝም ብለን ልንተወው አንችልም፣ አማራጫችን መጋፈጥ ነው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የሕዝብን ጥቅም እና መብት ለማስከበር የማይፈልግ የለም ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ÷ ፍላጎታችንን በችሎታ ማሳካት ካልቻልን ፍላጎት ብቻውን ምንም ነው ብለዋል።